በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት መኖር እንዴት እንደሚገባ ታውቅ ዘንድ እጽፍልሃለሁ፤ ቤቱም የእውነት ዓምድና መሠረት፥ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ነው።(1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 3:15)
1BIBLE
በመጀመሪያ እግዚአብሔር.........................................

ሕግንና ነቢያት

 
  1. ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «እኔ ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም» ብሏል /ማቴ.5፡17/፤ ይህ ቃል ምን ማለት ነው?



1. ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «እኔ ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም» ብሏል /ማቴ.5፡17/፤ ይህ ቃል ምን ማለት ነው?


መልስ


በማቴ.5፡17 የተጻፈው ቃል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም የመጣው ሕግና ነቢያትን «ለመሻር» ሳይሆን «ሊፈጽም» እንደሆነ ያስረዳል፡፡ በዚህ ክፍል ጌታችን «ሕግና ነቢያት» የሚላቸው በብሉይ ኪዳን ውስጥ የሚገኙትን የሕግ መጻሕፍትንና የነቢያት መጻሕፍትን ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እነዚህን መጻሕፍት ሊሽር አልመጣም፡፡ ሆኖም ጌታ ሕግንና ነቢያትን ሊሽር ባይመጣም «ሊፈጸም» መምጣቱን ማስተዋል ይገባል፡፡ «ሊፈጽም መጥቷል» ሲባልም ፍጹም ሊያደርግ መጥቷል ማለት ነው፡፡ እርሱ ይህንን ለማድረግ መብቱም ሆነ ሥልጣኑ አለው፤ ምክንያቱም ቀድሞም ቢሆን ሕጉንና ትንቢቱን ለሰዎች የሰጠ እርሱ ነው፡፡ ስለሆነም ሕጉንም ሆነ ትንቢቱን አስመልክቶ እርሱ የሚናገረው እውነት ፍጹምነት አለው፤ በሙሴ ሕግና በነቢያት መጻሕፍት ውስጥ ስለ አንድ ሕግና ትንቢት ከተነገረው ቃል ይልቅ ስለዚያው ሕግና ትንቢት ኢየሱስ የተናገረው ነገር ፍጹም ነው፤ በሕጉና በነቢያት መጻሕፍት ውስጥ ያልተገለጠና ኢየሱስ የተናገረው ነገር ሕጉን ወደ ፍጹምነት ያመጣዋል፡፡ ይህንን ለመረዳት የሰንበትን ጉዳይ መመልከቱ ጠቃሚ ነው፡፡ በዘዳ.5፡15 ላይ «በሰንበት ምንም ሥራ አትሥሩ» ይላል፡፡ ይህ ሕግ በጥቅሉ የተነገረና አንዳንድ በተለየ መልክ ሊታዩ የሚችሉ ሥራዎችንና ምክንያታቸውን ያላካተተ ነበር፤ ለምሳሌ «በሰንበት መልካም መሥራትን» በተመለከተ ለይቶ የሚገልጸው ነገር የለም፤ አንድ ሰው እርቦት እሸት ቀጥፎ ቢበላ፣ ወይም በሰንበት አህያው ወይም በሬው ጉድጓድ ውስጥ ገብቶ ቢያወጣ፣ ወይም በእግዚአብሔር ኃይል በሰንበት ቢፈወስ፣ /ማቴ.12፡1፤ ሉቃ.13፡15፤ 14፡5፤ ዮሐ.7፡23/ ኃጢአት ነው ወይስ አይደለም? ለሚለው ጥያቄ ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት መልስ አይገኝም፤ ኢየሱስ ግን «የሰንበት ጌታ» ስለሆነ «በሰንበት መልካም መሥራት ተፈቅዷል» ለማለት ተችሎታል /ማቴ.12፡12/፤ ስለሆነም በሰንበት መልካም መሥራት መፈቀዱን በተመለከተ በሕጉ ውስጥ ያልተነገረውን በመናገር የሰንበት ጌታ የሰንበትን ሕግ ፍጹም አድርጎታል፡፡

«ሕግና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም» ማለትም እንዲሁ ነው፤ በዚያው ይህ ቃል በተነገረበት በማቴ.5 ውስጥ ጌታ ኢየሱስ «አትግደል» በሚለው ሕግ ላይ ተጨማሪ በማድረግ በወንድም ላይ መቆጣትና ጨርቃም፣ ደንቆሮ ማለት እንደሚያስፈርድ ሲናገር እናያለን /ቊ.21-22/፤ «አታመንዝር» በማለው ሕግ ላይም ሲጨምር «አይቶ መመኘትም» በልብ ማመንዘር እንደሆነ ይገልጣል /ቊ.27-28/፤ በሌላ በኩል ደግሞ «በውሸት አትማል ነገር ግን መሐላዎችህን ለጌታ ስጥ» የሚለውን ሕግ «ከቶ አትማሉ» በሚል ሕግ ይበልጥ ሲያጸናው እናያለን፤ እንደዚሁም «ዓይን ለዓይን ጥርስ ለጥርስ» የሚለውን ሕግ «ክፉውን አትቃወሙ...» በሚለው ሲለውጥ እናያለን /ቊ.38-39/፤ «ባልንጀራህን ውደድ ጠላትህን ጥላ» የሚለውን ደግሞ «ጠላቶቻችሁን ውደድ» በሚለው ሲተካ እናያለን /ቊ.43-45/፤ ስለዚህ ኢየሱስ ሕግንና ነቢያት ሊፈጽም መጣ ማለት በአንዳንዱ ላይ በመጨመር፣ ከሌላው ላይ በመቀነስ ሌሎችን ደግሞ በሌላ በመተካት ተገቢ የሆነውን መለኮታዊ ውሳኔ መስጠት መቻሉን ያስረዳል፡፡ እዚህ ላይ አብሮ መስተዋል ያለበት ሊፈጽም መጥቷል በሚባልበት ጊዜ በሕግና በነቢያት የተጻፈውን ሊታዘዝ መጣ ማለት አለመሆኑን ነው፤ እንዲሁም በሕግና በነቢያት የተጻፈው ሁሉ በእርሱ ፍጻሜ ሊያገኝ /ሊተረጐም/ መጣ ማለትም አይደለም፤ ነገር ግን ከላይ እንደተብራራው በሚጨምረው ላይ እየጨመረ የሚቀንሰውን እየቀነሰ የሚለውጠውን እየለወጠ የሚያስቀረውን እያስቀረ ሕጉና ነቢያቱን ፍጹም /የተሟላ/ ለማድረግ መምጣቱን ብቻ ያመለክታል፡፡

2. ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሕጉን ሊሽር ካልመጣ ሰው በሕግ መጽደቅ የማይችለው ለምንድነው?

ሕጉ በራሱ ምንም ችግር የለበትም፤ እንዲያውም ሕጉን በተመለከተ «ስለዚህ ሕጉ ቅዱስ ነው፤ ትእዛዛቲቱም ቅድስትና ጻድቅት በጎም ናት» የሚል እናነባለን /ሮሜ7፡12/፡፡ እንዲሁም «በእግዚአብሔር ፊት ሕግን የሚያደርጉ ይጸድቃሉ እንጂ ሕግን የሚሰሙ ጻድቃን አይደሉምና» የሚል ቃል እናገኛለን /ሮሜ2፡13/፡፡ ይህ ማለት ግን ሰው ሕግን በመጠበቅ መጽደቅ ይችላል ማለት አይደለም፡፡ ምክንያቱም ሰው በሕግ መጽደቅ ያልቻለው ሕጉ ስለተሻረ ሳይሆን ከሥጋ የተነሣ ሕጉን መጠበቅ ስለማይችል ወይም ስለተሳነው ነው፡፡ በሮሜ8፡7 ላይ «ስለሥጋ ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥል ነውና፤ ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛምና፤ መገዛትም ተስኖታል» ይላል፡፡ ሕግን መጠበቅ የማይችለው ደግሞ አንዳንድ ሰው ብቻ ሳይሆን ሥጋን የለበሰ ሁሉ ስለሆነ በገላ.2፡16 ላይ «ሥጋን የለበሰ ሁሉ በሕግ ሥራ ስለማይጸድቅ እኛ ራሳችን በሕግ ሥራ ሳይሆን በክርስቶስ እምነት እንጸድቅ ዘንድ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነናል» ይላል፡፡ አንዳንዶቹን ወይም ብዙዎቹን ሕግን ለመጠበቅ የሚጥሩና የሚችሉ ሰዎች ቢኖሩ እንኳ ሁሉንም ሕግ መጠበቅ የሚችል ግን አይገኝም፡፡ ሰው ከሕግጋቱ አንዱን መጠበቅ ካልቻለ ደግሞ በሁሉ በደለኛ ይሆናል፡፡ ይህም በያዕቆብ መልእክት ውስጥ «ሕግን ሁሉ የሚጠብቅ ነገር ግን በአንዱ የሚሰናከል ማንም ቢኖር በሁሉ በደለኛ ይሆናል» ተብሎ ተገልጿል /ያዕ.2፡10/፡፡ ስለዚህ ሥጋን የለበሰ ሁሉ ሕግን ሙሉ ለሙሉ ወይም መቶ በመቶ መጠበቅ አይችልም፡፡ በዚህም ምክንያት ሕግን በመጠበቅ ሊጸድቅ የሚችል ሰው አይኖርም፡፡ እግዚአብሔር ግን ፍቅር ስለሆነ ሰው ይጸድቅ ዘንድ የጸጋ መንገድን አዘጋጀለት፡፡ ይህም ጸጋ ሰው በሕግ ሥራ ሳይሆን ኢየሱስ ክርስቶስን በማመን የእግዚአብሔር ጽድቅ ማግኘት እንዲችል የሚያደርግ ነው፡፡www.ewnet.org.et/btm_files/FAQ1.htm


 
ከእርሱም የሰማናት ለእናንተም የምናወራላችሁ መልእክት። እግዚአብሔር ብርሃን ነው ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም የምትል ይህች ናት።(1ኛ የዮሐንስ መልእክት 1:5)
This website was created for free with Own-Free-Website.com. Would you also like to have your own website?
Sign up for free