ሰው ሁሉ ኃጢአተኛ ነው
«እናንተም ደግሞ የእውነትን ቃል፣ ይኸውም የመዳናችሁን ወንጌል ሰምታችሁ፣ ደግሞም በክርስቶስ አምናችሁ፣ በተስፋው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ፤»ብሏል /ኤፌ.1፡13/፡፡
ሰው ሁሉ ኃጢአተኛ ነው
ለሞት በሚያደርስ በሽታ እንደተያዙ የማያውቁ ሕሙማን ወደ ሐኪም ዘንድ ሄደው ለመታከምም ሆነ መድኃኒት ለማግኘት እንደማይንቀሳቀሱ ሁሉ ኃጢአተኛ መሆናቸውንና ኃጢአትም ዘላለማዊ ሞትን የሚያስከትል መሆኑን የማያውቁ ብዙ ሰዎች ስለመዳን መንገድ ለመረዳት ፍላጐት ላይኖራቸው ወይም ጊዜ ላይሰጡ ይችላሉ፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ግን ማንኛውም ሰው ኃጢአተኛ እንደሆነ እንደሚከተለው ይናገራል፡፡
- «ሁሉ ዐመፁ በአንድነትም ረከሱ፤ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም፤ አንድም እንኳ የለም»/መዝ.13፡3/፡፡
- «ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ፤ አስተዋይም የለም፤ እግዚአብሔርንም የሚፈልግ የለም፤ ሁሉ ተሳስተዋል፤ በአንድነትም የማይጠቅሙ ሆነዋል፤ ቸርነት የሚያደርግ የለም፤ አንድ ስንኳ የለም»/ሮሜ.3፡11-12/፡፡
- «... ልዩነት የለምና፤ ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና፤ የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሏቸዋል»/ሮሜ.3፡22-23/፡፡
ከእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እንደምንረዳው ማንኛውም ሰው ኃጢአተኛ እንደሆነ ነው፡፡ ሰው ሁሉ ኃጢአተኛ ሊሆን የቻለውም በኃጢአት ከወደቀው ከአንድ ሰው ማለትም ከአዳም የተወለደ በመሆኑ ነው፡፡ ኃጢአት ወደ ዓለም የገባውም በዚሁ በመጀመሪያው ሰው በኩል ነው፤ አዳም የተሰጠውን ትእዛዝ ቢተላለፍ ሞትን እንደሚሞት አስቀድሞ ተነግሮት ነበር /ዘፍ.2፡16-17/፡፡ ስለሆነም ትእዛዙን በተላለፈ ጊዜ ኃጢአት ወደ ዓለም ከመግባቱም ሌላ በኃጢአት ምክንያት የተፈረደው የሞት ፍርድ ለሰው ሁሉ ሊደርስ ችሏል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ሲናገር «ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ሞት፤ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ» ይላል /ሮሜ.5፡12/፡፡ ስለዚህ ማንኛውም ሰው በኃጢአት ከወደቀው ከመጀመሪያው ሰው ስለተወለደ ኃጢአተኛ ከመሆኑም ሌላ የሞት ፍርድ የተፈረደበትም ነው፡፡ ሆኖም እግዚአብሔር ለሰዎች ካለው ፍቅር የተነሣ ሰዎች ከዚህ ዘላለማዊ ፍርድ ይድኑ ዘንድ አንድ ልጁን አዳኝ አድርጎ ወደ ዓለም ልኳል፡፡
የእግዚአብሔር ፍቅር
እግዚአብሔር ጻድቅ ከመሆኑ አንጻር በኃጢአት ላይ የሚፈርድ እውነተኛ ፈራጅ የመሆኑን ያህል ኃጢአተኞችን ለማዳን የሚወድ የፍቅር አምላክም ነው፤ ይህ ፍቅሩ የተገለጠውም አንድ ልጁን ለእኛ በመስጠቱ ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን ሲገልጽ «በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና፤ ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና» ይላል /ዮሐ.3፡16-17/፡፡ ስለዚህ ኃጢአተኝነቱን ያወቀና በፍርድ ሥር እንዳለ የተረዳ አንድ ሰው ተስፋ ቈርጦ ከእግዚአብሔር ከመራቅ ይልቅ እግዚአብሔር ልጁን እስከመስጠት ድረስ እንደወደደው ሊገነዘብ ይገባል፡፡
ስለዚህ አንተም አንባቢ ሆይ አሁን ያለኸው በምንም ሁኔታ ውስጥ ቢሆን እግዚአብሔር ልጁን ስለ አንተ ለሞት አሳልፎ እስኪሰጥ ድረስ የወደደህ መሆኑን ልታውቅ ይገባሃል፡፡ ክርስቶስ በመስቀል ላይ የሞተው ሞት ይህን የእግዚአብሔርን ፍቅር ያስረዳል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ሲናገር «ገና ደካሞች ሳለን ክርስቶስ ዘመኑ ሲደርስ ስለ ኃጢአተኞች ሞቶአልና፡፡ ስለ ጻድቅ የሚሞት በጭንቅ ይገኛልና፤ ስለቸር ሰው ግን ሊሞት እንኳ የሚደፍር ምናልባት ይገኝ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቷልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል» ይላል /ሮሜ.5፡6-8/፡፡ እግዚአብሔር ይህን ያህል አንተን ኃጢአተኛውን የሚወድህ ከሆነ አንተ ደግሞ እርሱ የሚያቀርብልህን የፍቅር ጥሪ ልትቀበል ይገባሃል፡፡ እርሱ የሚጠራህ አንተን ከዘላለም ጥፋት ለማዳን ነው፡፡ ስለዚህ የቀረበልህን የፍቅር ጥሪ ብትቀበል ለዘላለም የምትድነው አንተው ራስህ ነህ፡፡
የኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት
ሰው ከኃጢአትና ከዘላለም ሞት እንዲድን እግዚአብሔር ያዘጋጀው የመዳን መንገድ አንድ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ነው /ዮሐ.14፡6/፡፡ ኢየሱስ የሚለው የጌታችን ስም ትርጉምም አዳኝ ማለት ነው፡፡ በማቴ.1፡21 ላይ «እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ» የሚለው ቃል ይህንን ያስረዳል፤ እርሱ ወደ ዓለም የመጣበት ዋነኛ ዓላማም ሰውን ለማዳን እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ሲያስረዳ «የሰው ልጅ የጠፋውን ለማዳን መጥቷልና /ማቴ.18፡11፤ ሉቃ.19፡10/፤ እንዲሁም «ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው» /1ጢሞ.1፡15/ ይላል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም የመጣበትን ይህንን ሰውን የማዳን ዓላማ ለመፈጸም እስከሞት ድረስ ታዝዟል፤ እርሱ በመስቀል ላይ የሞተው የሁላችንን ኃጢአት ተሸክሞና የሁላችን ምትክ ሆኖ ነው፤ «... እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ» /1ጴጥ.2፡24/ «አንዱ ስለሁሉ ሞተ፤ እንግዲያስ ሁሉ ሞቱ» /2ቆሮ.5፡14/ የሚሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቦች ይህን ያረጋግጣሉ፤ እርሱ ኃጢአት የሌለበት በመሆኑ ስለኃጢአተኞች መሞትና ኃጢአተኞችን ማዳን ተችሎታል፤ ኃጢአት ያለበት ማንም ቢሆን ይህን ማድረግ አልተቻለውም፡፡ ስለዚህ በሰማይም ሆነ በምድር ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ አዳኝ የለም፤ መጽሐፍ ቅዱስ ከእርሱ በቀር ሌላ አዳኝ እንደሌለ አስረግጦ ሲናገር «መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና» ይላል /የሐ.ሥ.4፡12/፡፡ ከኃጢአተኝነታቸው የተነሣ በሞት ፍርሃት ውስጥ ለሚኖሩት ሁሉ ይህን የኢየሱስ ክርስቶስን ብቸኛ አዳኝነት መስማት ታላቅ የምስራች ነው፡፡ ይህም «የመዳን ወንጌል» ይባላል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች ሲጽፍ «እናንተም ደግሞ የእውነትን ቃል፣ ይኸውም የመዳናችሁን ወንጌል ሰምታችሁ፣ ደግሞም በክርስቶስ አምናችሁ፣ በተስፋው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ፤» ብሏል /ኤፌ.1፡13/፡፡ ይህም ቃል የመዳን ወንጌልን ተቀብለው በክርስቶስ ያመኑት ሁሉ የዘላለም መዳንን ከማግኘታቸውም በላይ በመንፈስ ቅዱስ መታተማቸውንም የሚያረጋግጥ ነው፡፡
አንባቢ ሆይ! አንተም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ብቸኛ አዳኝነት የሚናገረውን ይህን የመዳን ወንጌል ልትቀበል ይገባሃል፡፡
መዳንን የምታገኘው በጸጋ ነው እንጂ መልካም ሥራን በመሥራትህ አይደለም፤
በኢየሱስ ክርስቶስ ስም መሰብሰብ
ስለጌታችን ስለኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት ሰምተው በእርሱ ያመኑና የዳኑ ሰዎች ከማያምኑት ተለይተው በሃይማኖት ድርጅቶች ስም ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም መሰብሰብ አለባቸው፡፡ ጌታችን በስሙ ስለመሰብሰብ ሲናገር «ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ እኔ በመካከላቸው እሆናለሁና» ብሏል /ማቴ.18፡20/፡፡ ከማያምኑት ተለይተው በኢየሱስ ስም የሚሰበሰቡትን እግዚአብሔር በዚያ ስፍራ ይቀበላቸዋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ከማያምኑት ስለመለየት በሚናገርበት ክፍል ውስጥ «ስለዚህም ጌታ፡- ከመካከላቸው ውጡና የተለያችሁ ሁኑ ርኵሱንም አትንኩ» ይላል፤ ሁሉን የሚገዛ ጌታ እኔም እቀበላችኋለሁ ለእናንተም አባት እሆናለሁ፤ እናንተም ለእኔ ወንድ ልጆችና ሴት ልጆች ትሆናላችሁ ይላል፡፡» በማለት ይናገራል /2ቆሮ.6፡17-18/፡፡ እንዲሁም በዕብ.13፡13 ላይ «እንግዲህ ነቀፌታውን እየተሸከምን ወደ እርሱ ወደ ሰፈሩ ውጭ እንውጣ» በማለት የአማኞች ስፍራ የት እንደሆነ በግልጽ ይነግረናል፡፡ ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም «እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ ወደ እኔ ኑ» በማለት ሰዎችን ወደ ራሱ ይጠራል /ማቴ.11፡28/፡፡
ስለሆነም የተወደድክ አንባቢ ሆይ በኢየሱስ በማመን ከዳንህ በኋላ በየትኛውም የሃይማኖት ድርጅት ስም ሳይሆን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ብቻ ከሚሰበሰቡ ቅዱሳን ጋር ኅብረት ለማድረግ ሳትዘገይ ወስን፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን የምታገኘው በስሙ በተሰበሰቡት መካከል ነውና፡፡ በእርሱም ደስታና ሰላም ዕረፍትም ታገኛለህ፡፡www.ewnet.org.et/btm_files/Medan1.htm