በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት መኖር እንዴት እንደሚገባ ታውቅ ዘንድ እጽፍልሃለሁ፤ ቤቱም የእውነት ዓምድና መሠረት፥ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ነው።(1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 3:15)
1BIBLE
በመጀመሪያ እግዚአብሔር.........................................

ቤተክርስቲያን

ቤተክርስቲያን[Assembly]

በክርስትና ስም በሚጠራው ዓለምም ሆነ ክርስቲያን ባልሆነው ዓለም «ቤተክርስቲያንን» በተመለከተ ያለው መረዳት መጽሐፍ ቅዱስ ከሚነግረን እውነት ጋር በሚፋለስበት በዚህ ዘመን ስለ ቤተክርስቲያን ያለውን ትክክለኛ ሐሳብ ማወቅ በብዙዎች ዘንድ የሚናፈቅ ሆኗል፡፡ በብዙ የዶክትሪን አስተሳሰቦች እና ሥርዓተ አምልኮዎች የሚለያዩና በተለያዩ ስያሜዎች የሚጠሩ አብያተ ክርስቲያናት በበዙበት በዚህ በያዝንው ክፍለዘመን የቤተክርስቲያንን ትክክለኛ ማንነት ለማወቅ የተጠማውን የሰዎችን ኅሊና የሚያረካ እውነት መገኘት የሚችለው ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ከተጻፈው ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ወደ 150 ጊዜ ያህል ተጠቅሶ የሚገኝ በመሆኑ የቤተክርስቲያን ትክክለኛ ገጽታ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በስፋት ይገኛል፤ የመንፈስ ቅዱስን ምስክርነት በውስጥ ጆሮአችን እያዳመጥን ብናነበው ስለ ቤተክርስቲያንም ሆነ ስለሌሎች ታላላቅ መንፈሳውያን ርእሶች የተገለጠ እውነትን እናገኝበታለን፡፡

የቤተክርስቲያን ማንነት

«ቤተክርስቲያን» የሚለው ቃል በግሪክ ቋንቋ «ኤክሌሲያ» ለሚለው ቃል የተሰጠ ትርጉም ሲሆን ኤክሌስያ ማለትም «የተጠራች ጉባዔ» ማለት ነው፡፡ በግእዝም ቤተክርስቲያን የሚለው ቃል የክርስቲያን ቤት የሚል ፊደላዊ ፍቺ ቢኖረውም ዋነኛ ሐሳቡ «የክርስቲያን ወገን» ማለት ስለሆነ ኤክሌስያ የሚሰጠንን ስሜት በተወሰነ ደረጃ ይዟል፤ በብሉይ ኪዳን ዘመን በምድር ላይ የነበረችው በእግዚአብሔር የተመረጠች ጉባዔ ቤተእስራኤል ነበረች፡፡ ይህችም ጉባዔ ማለትም እስራኤል፣ ኤክሌሲያ ተብላ የተጠራችበትን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ እናገኛለን/የሐ.ሥ.7፡38/፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በአሕዛብ አገርም በአንድ ምክንያት የሚሰበሰብ ትልቅ ጉባዔ ኤክሌስያ ይባል ነበር/የሐ.ሥ.19፡3/፡፡ እነዚህ በቤተ እስራኤልም ሆነ በቤተ አሕዛብ የነበሩት ጉባዔያት ምድራውያን ሲሆኑ በወንጌል ቃል በኩል ከዚህ ዓለም የተጠሩት ክርስቲያኖች ጉባዔ /ኤክሌስያ/ ግን ሰማያዊ ባሕርይ ያላት ጉባዔ ናት፤ ሐዋርያው ጳውሎስ «... ብዙ ልዩ ልዩ የእግዚአብሔር ጥበብ አሁን በቤተክርስቲያን በኩልበሰማያዊ ስፍራ ውስጥ ላሉት አለቆችና ሥልጣናት ትታወቅ ዘንድ...» /ኤፌ3፡10/ ብሎ ከጻፈው ቃል ውስጥ ይህንን የቤተክርስቲያንን ሰማያዊ ባሕርይ እንረዳለን፡፡ በብሉይ ኪዳን የነበረችው የተጠራች የእግዚአብሔር ጉባዔ በሥጋ ከአብርሃም ዘር የሆኑትን ብቻ ያካተተች ጉባዔ ነበረች፡፡ በአዲስ ኪዳን ያለችው የእግዚአብሔር ጉባዔ (ኤክሌስያ) ግን ከቤተ እስራኤል ብቻ ሳይሆን ከቤተ አሕዛብም የሆኑትን ወገኖች ያቀፈች ጉባዔ ናት፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ «ከእነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆችን ሊያስነሣለት እግዚአብሔር ይችላል» ብሎ «አብርሃም አባት አለን» እያሉ ለሚመኩት ፈሪሳውያን በተናገረው መሠረት /ማቴ.3፡9/ ከቤተ አሕዛብ መካከል በኢየሱስ ክርስቶስ ያመኑ ሁሉ የአብርሃም ልጆች ለመሆን ችለዋል፡፡ ጳውሎስም ክርስቶስ ኢየሱስ በእንጨት ላይ የተሰቀለው አሕዛብን በእርሱ በኩል ወደ አብርሃም በረከት ውስጥ ለማስገባት እንደሆነ ሲናገር «በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፏልና ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን የመንፈስን ተስፋ በእምነት እንድንቀበል የአብርሃም በረከት ወደ አሕዛብ በእምነት ይደርስላቸው ዘንድ» ብሏል /በገላ.3፡14/፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያንን የመሠረተው ከቤተ እስራኤልና ከቤተ አሕዛብ በተጠራ አዲስ ሕዝብ ነው፡፡ በመስቀል ላይ የመሞቱም ዓላማ ይህንኑ አዲስ ሕዝብ ይፈጥር ዘንድ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ሲገልጥ «እርሱ ሰላማችን ነውና ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳ በሥጋው ያፈረሰ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው» ይላል/ኤፌ.2፡11-16/፡፡ ከዚህም እንደምንረዳው በአዲስ ኪዳን ሰዎችን የእግዚአብሔር ሕዝብ የሚያደረገው በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ነው እንጂ እስራኤላዊ እና አሕዛባዊ የመሆን ጉዳይ አይደለም፡፡ ስለዚህ የቤተክርስቲያን አባላት ከፀሐይ መውጫ እስከ ፀሐይ መጥለቂያ ድረስ ካሉት ነገዶች ሁሉ በኢየሱስ ክርስቶስ በእውነት ያመኑት ሁሉ ናቸው፡፡

በመሆኑም «በአይሁዳዊና በግሪክ ሰው መካከል ልዩነት የለምና፤ አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና፤ ለሚጠሩትም ባለጠጋ ነው፤ የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና» /ሮሜ.10፡12/ የሚለው ቃል የገባቸው አማኞች በምድራቸውም ሆነ በሌሎች የውጭ አገሮች ውስጥ ሰዎች በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው መሰብሰባቸውን ይናፍቃሉ፤ እንዲህ ያሉት አማኞች በዓለም ካሉት ነገዶች ሁሉ ሰዎች በክርስቶስ አምነው በስሙ የመሰባሰባቸውን ዜና ሲሰሙ ደስታና መንፈሳዊ ሐሴት ይሞላባቸዋል፡፡ እንደዚሁም በዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ እንደተመዘገበው የምስጋና ቃልም «መጽሐፉን ትወስድ ዘንድ ማኅተሙንም ትፈታ ዘንድ ይገባሃል፤ ታርደሃልና በደምህም ለእግዚአብሔር ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ሰዎችን ዋጅተህ ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት ይሆኑ ዘንድ አደረግሃቸው፤ በምድርም ላይ ይነግሣሉ» እያሉ በጉን /ጌታ ኢየሱስን/ ያመሰግኑታል /ራእ.5፡9/፡፡

«ቤተክርስቲያን» የሚለው ቃል ከሕዝብና ከአሕዛብ መካከል እግዚአብሔር የጠራቸውንና የመረጣቸውን የአዲስ ኪዳን አማኞችን ጉባኤን የሚያመለክት ሆኖ ሳለ ክርስቲያኖች ለመንፈሳዊ ጉዳዮች የምንሰበሰብበትን ቦታ ወይም አዳራሽ እንደዚሁም ራሳችን ስም አውጥተን የፈጠርነውን የእምነት ድርጅት እንዲያመለክት አድርገን መጠቀም ከቃሉ ቀጥተኛ ትርጉም ውጭ መሆን ነው፡፡ እግዚአብሔር ቤተክርስቲያኑን የዋጃት በገዛ ደሙ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ሲያስረዳ «... በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን ትጠብቋት ዘንድ ...» ይላል /የሐ.ሥ.20፡28/፡፡ ቤተክርስቲያን ሕንፃ ወይም ድርጅት ከሆነች ደግሞ ክርስቶስ ለሕንፃ ወይም ለድርጅት ሞቷል ማለት ሊሆን ነው፤ ሆኖም በመጽሐፍ ቅዱስ ቤተክርስቲያን የሚለው ቃል በሚገኝበት በማናቸውም ጥቅስ ውስጥ በምድር ላይ ሰማያዊ ጠባይን ተላብሳ የምትገኘውን የተመረጠች የእግዚአብሔርን ጉባዔ ከማመልከት በቀር በአንድም ስፍራ ሕንፃን ወይም ድርጅትን አያመለክትም፡፡ እንዲህ ሲባል ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን ለማምለክና ቃሉን ለመስማት የሚሰባሰቡበት ቤት እንዲሁም እንደ የአገሩ ሕግ ለመሰብሰብ ሆነ ለሕዝብ መንፈሳዊ አገልግሎትን ለመስጠት የሚያስችላቸውን መንፈሳዊ ድርጅት ማቋቋም አይችሉም ማለት አይደለም፤ ይሁን እንጂ ሕንፃውም «ሕንፃ»፣ ድርጅቱም «ድርጅት» ሊባል ይችላል እንጂ «ቤተክርስቲያን» ሊባል አይችልም፡፡ ለምሳሌ በፊልሞና ቤት ውስጥ ትሰበሰብ ስለነበረችው ቤተክርስቲያን በፊልሞና መልእክት መግቢያ ላይ «በቤትህም ላለች ቤተክርስቲያን» የሚል ቃል እናነባለን /ፊል.2/፡፡ በዚህ ንባብ ውስጥ ቤተክርስቲያን በፊልሞና ቤት ስለተሰበሰበች የፊልሞና መኖሪያ ቤት «ቤተክርስቲያን» ተብላ እንዳልተጠራች እናያለን፤ በዚያ በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ለቤተክርስቲያን መሰብሰቢያ ተብሎ ሕንፃ መሥራትም አልተጀመረም ነበር፡፡ ቤተክርስቲያን ትሰበሰብ የነበረው ከአማኞች መካከል ቤታቸውን ለዚህ አገልግሎት በሰጡ ወይም በፈቀዱ ሰዎች ቤት ውስጥ ነበር፡፡ ለምሳሌ የማርቆስ እናት ማርያም በኢየሩሳሌም/የሐ.ሥ.12፡5-12/፣ አቂላና ጵርስቅላ በሮሜ /ሮሜ16፡3-5/፣ ፊልሞና በቈላስይስ /ፊልሞ2፣11፤ ቈላ.4፡9/፣ ንምፉን በሎዶቅያ /ቈላ.4፡15/ ቤታቸውን ለቤተክርስቲያን መሰብሰቢያ እንዲሆን ከፈቀዱት መካከል የሚጠቀሱ /ቅዱሳን/ ሰዎች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ በቤታቸው የምትሰበሰበው የምእመናን ኅብረት ቤተክርስቲያን ተባለች እንጂ የአንዳቸውም መኖሪያ ቤት «ቤተክርስቲያን» ተብሎ አልተጠራም፡www.ewnet.org.et/btm_files/aclesia.htm


 
ከእርሱም የሰማናት ለእናንተም የምናወራላችሁ መልእክት። እግዚአብሔር ብርሃን ነው ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም የምትል ይህች ናት።(1ኛ የዮሐንስ መልእክት 1:5)
This website was created for free with Own-Free-Website.com. Would you also like to have your own website?
Sign up for free