በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት መኖር እንዴት እንደሚገባ ታውቅ ዘንድ እጽፍልሃለሁ፤ ቤቱም የእውነት ዓምድና መሠረት፥ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ነው።(1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 3:15)
1BIBLE
በመጀመሪያ እግዚአብሔር.........................................

ጴንጤነት ካረጀ………..?

ወንዱ ብስራት 

                     እኔን ጨምሮ የብዙዎች ጥያቄ ይመስለኛል፡፡ አሁን ከዓለም ከወጡት መጤ ጴንጤ በቀር የቆየው ጉዱን ያውቀዋል፡፡ ድግግሞሽ ሥርዓት ነው፡፡ በኮንፈረንስ ብዛት እራሳችንን እየሸነገልን የኖርንበት፡፡ በስብከትና በትንቢት ስብቀት በማይጨበጥ የተሐድሶ ተስፋ ተለጉመን እያቃሰትን ያዘገምንበት፡፡ ጴንጤነት፡፡

«ተስፋ አልቆረጥኩም ትንሽ ላጨብጭብ ፣ ልጨፍር ፣ ልዘምር» ያለ ይቀጥል፡፡ ከዚያ ፍንክች እንዳይል፡፡ የማይታበለው ሐቅ መዳኑን አግኝቶአልና ቅድስናውን ሳያስነካ ይቀጥል፡፡ በምድር ካለ ግን እግዚአብሔርን በሕይወቱ አክብሮ ማለፍ የሚፈልገውና እዚያ ያለው ስሜታዊ ግርግር ብቻ የሰለቸውስ? እርሱ የት ይደርስ? በዚያ መንፈሳዊ በሚመስል እንቅስቃሴ ውስጥ ራሱን የሰወረውን ክፋት እያየ ልቡ ሲደማ የኖረ አማራጩ ምን ይሁን?

እዚያው ተሐድሶ ይመጣል አንል ነገር፣ እርሱ የሚመጣው በሰው በተለይም በአገልጋይ ነውና ይህን ደግሞ ጭላንጭሉን ማየት ከብዶአል፡፡ መሪዎች ከፍተዋል፡፡ አገልጋዮች በእግዚአብሔር አስራትና በህዝብ መባ ከዲፕሎማ ጀምረው እስከ ዶክትሬት በቲኦሎጂና በስነ አመራር ለራሳቸው ዲግሪዎችን ለመሰብሰብ ወረፋ ገብተዋል፣ ህዝቡን ግን ከመድረክ አገልግሎትና ከትንሽ እንቅስቃሴ በቀር በእረኝነት ማገልገሉን እርግፍ አድርገው ትተውታል/ ሕዝ 34/፡፡ ይህ ደግሞ በኀጢአት ድፍረትም እየታገዘ ሳለ ተሐድሶ እንዴት ይጠበቃል? ብሔራዊም ሆነ አለምአቀፋዊ መከራ በአዲስ ኪዳን ብዙም አያስኬድ፡፡
ታዲያ ሐይማኖት ሰልችቶን ሐይማኖት እንቀይር? ብዙዎች ወደ ዓለም እየተሰናከሉ ሲመለሱ አንዳንዶች ወደ ኦርቶዶክስ «ይቅር ለቤቴ» ማለት ጀምረዋል፡፡ ከድጡ ወደ ማጡ! ወደ ዓለም መሔድ ደግሞ ወደ ገሃነም ነውና አይመረጥም፡፡

ወደ ኦርቶዶክስ መመለስን የራስዋ ልጆች የፃፉትን እነ «ገድል ወይስ ገደል?» መፅሀፍ ያነበበ እንዴት አድርጎ ይሞክረዋል? ወደዚያ ክስረትና ኑፋቄ? NO!
ታዲያ አማራጩ ምንድነው? ወደ ኢየሱስና መፅሀፍ ቅዱስ መመለስ ብቻ ነው፡፡ አሁን «ኦርቶዶክስነት፣ ሙሉወንጌልነት፣ ካቶሊክነት፣ ጴንጤነት ወዘተ ሰለቸኝ ካልክ» እንኩዋን ሀይማኖት ሰለቸህ! ተመለስና ደቀመዝሙር ሁን፡፡

ስላሴን እመን፣ በኢየሱስ አዳኝነት ላይ ተመርኮዝ፣ በመንፈስ ቅዱስ አጽናኝነት፣ መሪነትና አስተማሪነት ላይ ተመርኩዘህ መፅሀፍ ቅዱስህን ጓደኛ አድርገህ ወገብህን ታጠቅ፡፡ «ሐይማኖትህ ምንድነው?» ሲሉህ «የጌታ ደቀመዝሙር እንጂ ሌላ አይደለሁም » በላቸው፡፡

ምክንያቱም ጌታ በመጨረሻው ለሐዋሪያት ያዘዘው፡-« ስለዚህ ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀመዛሙርት አድርጓቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ አስተምሯቸው፣ እኔም እስከ አለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ» ብሏል ማቴ 28፡19-20፡፡ ልብ አድርጉ፡- ጌታ ደቀመዛሙርት አድርጉ እንጂ ጴንጤ ፣ ሙሉወንጌል፣ገነት፣ መሰረተክርስቶስ ፣ ባፕቲስት፣ ኦርቶዶክስ፣ካቶሊክ አድርጉልኝ አላለም፡፡ ሰዎች ግን እራሳቸው በሰሩት በረት ውስጥ እያጎሩ ለራሳቸው በሚያመች መንገድ ቀርፀውናል እንጂ ደቀመዛሙርት አላደረጉንም፡፡ አማኞች ብንሆንም የቤተእምነቶች እንጂ የጌታ ደቀመዛሙርት አልሆንም፣ የእነ «ፓስተር እገሌ » እና የእነ «ነብይ እገሌ» ወይም የእነ «ሐዋሪያው እገሌ» ደቀመዛሙርት ነው እየሆንን ያለነው፡፡

«ሕብረት አያስፈልግም ወይ?» ትሉኝ ይሆናል፡፡ በደንብ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ጌታ «ሁለት ወይም ሶስት በስሜ በሚሰባሰቡበት መካከል በዚያ እገኛለሁና» እንዳለን ቃሉን እንመን፡፡« በምድር ላይ ሁለት ሆናችሁ ስለምንም ነገር በመስማማት ብትጠይቁ በሰማይ ያለው አባቴ ያደርግላችኋል» ያለንን ቃል አምነን እንቀበል /ማቴ 18፡19-20/፡፡ ይህ ለስነ ስርዓት እርምጃ ብቻ እንደሆነ አንውሰደው፡፡ ሁለት ደቀመዛሙርት በመካከላቸው ስምምነት ካለ የማሰርና የመፍታት ስልጣን ሳይቀር እንዳላቸው ልንቀበል ይገባል /ማቴ 18፡18/፡፡ ስምምነት ግን ወሳኝ ነው፡፡ ዐውዳዊ የማቴ 18 አሰሳን ብንመለከት ቁ. 1 ፉክክር በሐዋርያቱ መካከል መኖሩን ፣ ቁ.5 እርስበርስ መቀባበል እንደሚገባን፣ ቁ.10 እርስበርስ መናናቅ እንደማይገባ፣ ቁ.15-35 በደል ቢኖር ተወቃቅሶ ይቅር መባባል እንደሚገባ ያስተምራል፡፡በፕሮቴስታንት ዓለም በጎ ያልሆነ ፉክክር የተለመደ ነው፡፡ አንዱ አዳራሽ ተከራይቶ ሰው ከሰበሰበ ሌላውም «እኔም ጌታ ተናግሮኛል» ብሎ ይቀጥላል፡፡

አዳማጭ የለም፣ ሁሉ ታናጋሪ ነው፣ ሁሉ ባለመድሐኒት፡፡ የብዙዎች አንደበት ተስሎአል፡፡ አራሚ እንጂ ከእኔ ጭምር ታራሚ ለመሆን የሚፈልግ የለም፡፡መቀባበል የለም፡፡ መናናቅ ከተጀመረ ቆይቷል፣መዘረጣጠጥ፡፡ ድሮ በፕሮቴስታንቱ ላይ ከኦርቶዶክሳውያን ድንጋይ ይወረወር ነበር፡፡ አሁን ደግሞ በተራው በእያንዳንዱ ጴንጤ እጅ የማይታይ ድንጋይ አለ፣እርስበርስ የምንወራወረው፡፡ እጅ ማለቴ ምላስ ለማለት እንደሆነ ይታወቅልኝ፡፡

ይቅር መባባል አቅቶን ሁለት አብያተእምነት ከ10 ዓመታት በላይ በፍርድ ቤት እርስበርስ ተካስሰናል፡፡ በመንግስት ጣልቃ ገብነት ነገሩ ውሳኔ አግኝቶ ካለ በኋላ እንኩዋ እርስበርስ የተነጣጠሉ አሉ፡፡ በዚህ ውስጥ ሆነን ነው እንግዲህ «አገር አማን ነውና ዝም በሉ!» የምንባለው፡፡ ስምምነት ሳይኖር የእግዚአብሔር እጅ ይያዛል፡፡ ወይ በንስሃ እስክንመለስ አሊያም ደግሞ ሙት ሀይማኖት ሆነን እስኪያበቃልን አጋንንት በመካከላችን ይጮኻልና በዚህ አትደነቁ፡፡

የሆነው ሆኖ ከሙት ኃይማኖተኝነት ወደ ደቀመዝሙርነት መመለስ ይበጀናል፡፡ ጴንጤነት አርጅቷል ፣ እንቅስቃሴው ተሸምድዶ ያበቃለት የጫጫታ አዙሪት ሆኗል፡፡ ከኦርቶዶክስነትም ፣ ከካቶሊክነትም ሆነ ከፕሮቴስታንትነት የቀደመው ሐዋርያዊ እንቅስቃሴ ማለትም ደቀመዝሙርነት ግን ሳያረጅ ይኖራል፡፡

https://www.facebook.com/permalink.php?story_fbid=673768892668304&id=521450271233501


 
ከእርሱም የሰማናት ለእናንተም የምናወራላችሁ መልእክት። እግዚአብሔር ብርሃን ነው ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም የምትል ይህች ናት።(1ኛ የዮሐንስ መልእክት 1:5)
This website was created for free with Own-Free-Website.com. Would you also like to have your own website?
Sign up for free