የቤተክርስቲያን ሥልጣን
በማቴ 18፡15-20 ውስጥ «አክሌሲያ» የሚለው ቃል ለሁለተኛ ጊዜ ተጠቅሶ የሚገኝ ሲሆን በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ይህን ክፍል እናጠናለን፤ በዚህ ስፍራ ላይ ቤተክርስቲያን የተጠቀሰችው ከሥነሥርዓትና በምድር ላይ ካላት የአስተዳደር ሥልጣን ጋር በተያያዘ መልኩ ነው፡፡ ይህም በየስፍራው ወይም በአጥቢያ ደረጃ በተሰበሰበ ጉባኤ የሚታየው የቤተክርስቲያን ገጽታዋ ነው፤ ንባቡም እንደሚከተለው ነው፤ «ወንድምህ ቢበድልህ ሄደህ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ውቀሰው፤ ቢሰማህ ወንድምህን ገንዘብ አደረግኸው፤ ባይሰማህ ግን በሁለት ወይም በሦስት ምስክር አፍ ነገር ሁሉ እንዲጸና ዳግመኛ አንድ ወይም ሁለት ከአንተ ጋር ውሰድ፤ እነርሱንም ባይሰማ ለቤተክርስቲያን ንገራት፤ ደግሞ ቤተክርስቲያንን ባይሰማት እንደ አረመኔና እነደ ቀራጭ ይሁንልህ፡፡ እውነት እላችኋለሁ፤ በምድር የምታስሩት ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድር የምትፈቱት ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል፡፡ ደግሞ እላችኋለሁ ከእናንተ ሁለቱ በምድር በማናቸውም በሚለምኑት ነገር ሁሉ ቢስማሙ በሰማያት ካለው ከአባቴ ዘንድ ይደረግላቸዋል፡፡ ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና» /ማቴ.18፡15-20/፡፡
እግዚአብሔር በምድር ላይ ራሱን የሚገልጠው በቤተክርስቲያኑ በኩል በመሆኑና ቤተክርስቲያንም በምድር ላይ የእግዚአብሔር መለኮታዊ ፈቃድ የሚገለጥባት ማዕከል በመሆኗ በእርሱ ፊት ተቀባይነት ያለውን ውሳኔ መወሰን እንድትችልም ሥልጣን እንደተሰጣት ከሚያመለክቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባቦች መካከልም ከላይ የተጠቀሰው አንዱና ዋንኛው ነው፡፡ በዚህ ምንባብ ውስጥ ጌታችን ለቤተክርስቲያን የሰጠውን ሥልጣን ለመገንዘብም በቅድሚያ በምንባቡ ውስጥ ያሉትን ሐሳቦች አንድ በአንድ መመልከቱ ጠቀሚ ነው፡፡
ወንድምህ ቢበድልህ ...
ጌታ ኢየሱስ በዚህ ንባብ ውስጥ የገለጸው በዳይ፣ ለተበዳዩ በእምነት ወንድም የሚሆን አማኝ ወይም ክርስቲያን በመሆኑ አንድ አማኝ ከማያምን ሰው የሚደርስበት የበደል ጉዳይ በዚህ ምንባብ የሚታይ አይደለም፤ በመሆኑም ምንባቡ ሙሉ በሙሉ በአማኞች መካከል ስላለ ጉዳይ የሚናገር እንደሆነ መገንዘቡ ጠቃሚ ይሆናል፤ በዚሁ ምዕራፍ ማለትም በማቴ.18፡3 ላይ ጌታ ተመልሰው እንደ ህፃናት ስለሚሆኑ የመንግሥተ ሰማያት ወራሾች ይናገራል፤ በቊ.6 እና 10 ላይም በኢየሱስ ስለሚያምኑ ታናናሾች ይናገራል፡፡ በመሆኑም ከመጀመሪያው ቊጥር ጀምሮ ንባቡ ስለ አማኞች እንጂ ስለ ኢአማንያን የሚናገር አይደለም፡፡ ስለዚህ «ወንድምህ ቢበድልህ ...» እየተባለ መመሪያ የሚቀበለው ሰውም ሆነ የበደለው ወንድም ሁለቱም በክርስቶስ ወንድማማች የሆኑ ሰዎች ናቸው፤ ይህም በደል በግልጥ የተደረገ በደል ሊሆን ይገባዋል፤ በደል ስለመኖሩ እርግጠኝነት በሌለበትና ሳይበድለኝ አይቀርም የሚባልበት ሁኔታም በዚህ አልተካተተም፤ ሁለቱ አማኞች እርስ በእርስ የተበዳደሉ ከሆኑም ጉዳያቸው ከዚህ ምንባብ ሽፋን ውጪ ነው፤ በብዙዎች ዘንድ የሚታወቅ በደልም በዚህ አልተካተተም፤ ይህ አንድ አማኝ በሌላው አማኝ ላይ የሚያደርሰው የግል በደል ነው እንጂ የቤተክርስቲያን ጉዳይም አይደለም፡፡ ስለሆነም ይህ ቃል አንድ አማኝ ያለጥርጥር በሌላው ባልበደለው አማኝ ወንድሙ ላይ በደል ሲያደርስ ማለትም በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የወንድሙን መብት ቢጋፋ፣ አለአግባብ በወንድሙ ላይ ማናቸውንም ጉዳት ቢያደርስና ወንድሙን ቢያሳዝነው ይህንን የተፈጠረውን ችግር ለማስወገድና ፍቅርን ወደነበረበት ለመመለስ እንዲቻል ጌታችን ያስተማረው ነው፡፡ ከላይ የተጠቀሰው ምንባብ አራት ደረጃዎች አሉት፤ እነርሱ:-
1. አማኙ በደለኛውን ወንድም ለብቻቸው ሆነው ሳሉ እንዲወቅሰው፣
2. ለብቻው ካልሰማው ከእርሱ ጋር አንድ ወይም ሁለት ሰዎችን ይዞ በአንድነት እንዲወቅሱት፣
3. በሁለት ወይም በሦስት ሰዎች ፊት ሊመለስ ካልቻለ ለቤተክርስቲያን እንዲነግራት፣ ቤተክርስቲያን እንድትገሥጸው፣
4. በዚያም የማይመለስ ከሆነ ውሳኔ እንድትሰጥበት የሚናገሩ አራት ደረጃዎች ናቸው፡፡
እነዚህንም አራት እርምጃዎች እንደሚከተለው ከፋፍለን እንመከታቸዋለን፡፡
1. ሄደህ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ውቀሰው
በዚህ ደረጃ ወደ በዳዩ የሚሄደው ተበዳዩ ነው፤ ይህም በትክክል ጸጋን የሚያመለክት ነው፤ የበደለው የሰው ልጅ ሆኖ ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቀው ዘንድ ኃጢአተኛውን ሊፈልግ የመጣው ጌታ ለተበደለው ደቀመዝሙሩ የሚሰጠው መመሪያም ወደ በዳዩ መሄድን ነው እንጂ በዳዩ ወደ እርሱ እንዲመጣ አይደለም፤ ይህ የጌታ የኢየሱስ መንገድ ነው፡፡ እንደ ዓለም ሥርዓት ከሆነ በዳዩ ወደ ተበዳይ እንዲሄድ ይጠበቅበታል፤ አለም ኩራተኛ ናትና ዕርቅን የምትፈልግበት ዋና ምክንያትም ፍቅርን ለመመለስና በዳዩን ለማቅናት ሳይሆን በደለኛውን ለመቅጣትና ተበዳዩን ለመካስ በመሆኑ ይህንን የምታስፈጽምባቸው መንገዶችም ክርስቲያኖች ከሚከተሉት መንገድ በእጅጉ የራቀ ነው፡፡ እንደጌታ መንገድ ወደበዳዩ የሚሄደው ተበዳዩ ነው፤ ከልቡ ፍቅር የራቀውን በደለኛ የሚፈልገው ተበዳዩ ነው፤ ወደበደለው ወንድሙ የሚሄደውም ካሳ ፈልጎ ሳይሆን የጠፋውን ፍቅር ሊመልስ ወንድሙንም እንደቀድሞው ገንዘቡ ሊያደርገው ነው፡፡ ይህንንም ለማድረግ ለብቻቸው ባሉበት ተበዳይ በዳዩን እንዲወቅሰው ታዟል፤ እዚህ ላይም የጌታ መንገድ ከዓለም መንገድ ይለያል፤ እኛ በተበደልን ጊዜ ስለመበደላችንና ስለበደለን ሰው ለሌላው ወንድም ወይም እህት ማውራት ይቀልለናል፤ ይህ ደግሞ የሻከረውን ፍቅር ፈጽሞ አደጋ ላይ ከሚጥሉ የሥጋ መንገዶች ዋንኛው መሆኑን የሚክድ ማን ነው? የበደለንን ሰው ወደ ጎን በመተው ሌሎች ከእኛ ጋር ሆነው ለእኛ እንዲያዝኑልን ወይም በበደለን ሰው ላይ እንዲፈርዱ የመፈለግ ሐሳብ በራሱ ሥጋዊ ነው፤ ውጤቱም የበደለውን ሰው ከእኛም ሆነ ከሌሎች ማራቅ ነው፤ ይህ ወንድምን ገንዘብ ለማድረግ ከመፈለግ በእጅጉ የራቀ የጥላቻ አካሄድ ነው፤ በመሆኑም በዚህ በመጀመሪያው ደረጃ የበደለንን ሰው መውቀስ ያለብን ለብቻችን በምንሆንበት ቦታ ነው፤ በዚያም ብቻችንን በምንሆንበት ስፍራ ለበደለን ወንድም እንዴትና እንደምን እንደበደለን በፍቅርና በትህትና እናስረዳዋለን፤ ይህ በፍቅር በዳዩ በደሉን እንዲያውቀው የምናደርግበት መንገድም ደብዳቤ በመጻፍ ሳይሆን ፊት ለፊት በመገናኘትና በመነጋገር ነው፤ «ውቀሰው» ተብሎ የተተረጎመው ቃል ትክክለኛ ፍቺም ይኸው ነው፡፡ በዚህ ከተሳካልንና በዳዩ በደሉን ለማመን ከቻለ ጌታ እንዳለው ገንዘብ እናደርገዋለን፤ ሆኖም ግን በዳዩ ይህን መንገድ የማይቀበል ከሆነ አማራጩ መንገድ በሁለተኛ ደረጃ የተጠቀሰውን እርምጃ መውሰድ ነው፡፡
2. አንድ ወይም ሁለት ከአንተ ጋር ውሰድ
በሁለተኛ ደረጃም ከአማኞች አንድ ወይም ሁለት ከራሱ ጋር በመውሰድ ዳግመኛ ተበዳዩ ወደበዳዩ በመሄድ አብረውት ካሉት ጋር በዳዩ እንደበደለ ለማስረዳት በመጀመሪያ እንዳደረገው በጸጋ ጥረት እንዲደረግ ጌታ አስተምሮናል፡፡ የዚህ ጥረት ዓላማም እንደመጀመሪያው ሁሉ ወንድምን ገንዘብ ለማድረግ ነው፡፡ ሆኖም በዚህም ባይሳካ ወደ ሦስተኛው እርምጃ እንድንገባ ጌታ ፈቅዶልናል፤ ይህም ለቤተክርስቲያን መንገር ነው፡፡
3. ለቤተክርስቲያን ንገራት
የቤተክርስቲያን ጥረትም እንደቀደሙት ሁሉ በጸጋ ነገሮችን ወደነበሩበት የፍቅርና የወንድማማችነት መንፈስ መመለስን ዓላማው ያደረገ ሊሆን ይገባዋል፤ በተጨማሪም የቤተክርስቲያንን ወቀሳ /ምክር እና ተግሣጽ/ ለመስማት የሚመጣው በደለኛ ወንድም በግል የተወቀሰና ወቀሳውን ያልሰማ ከመሆኑም ባሻገር በሁለት ወይም በሦስት ወንድሞችም ሊመለስ አለመቻሉ በደለኛነቱን እርግጠኛ ያደርገዋልና ቤተክርስቲያን የመጨረሻውን ወቀሳ ለመስጠት ሕጋዊ መሠረት ይኖራታል ማለት ነው፡፡ እንደሚታወቀው ሁሉ የመጨረሻ ምክርና ተግሣጽ የሚሰጠውና ይህንንም ተግሣጽ በደለኛው ካልሰማ የመጨረሻውን ውሳኔ መስጠት የሚችለው «ከፍተኛ ባለ ሥልጣን» የሆነ አካል ነው፤ ጌታችንም አካሉ የምትሆን ቤተክርስቲያንን ወቀሳ እንድትሰጥና አስፈላጊውን የመጨረሻ ውሳኔ እንድትወስን መመሪያ ሲሰጥ ቤተክርስቲያንን በምድር ላይ ከፍተኛ ባለሥልጣን ማድረጉን እንረዳለን፡፡ ይህም ወቀሳ ምክር አዘል ተግሣጽ እንደሆነ መረዳት አያዳግትም፡፡ ቤተክርስቲያንም በደለኛውን ለመውቀስ የሚያስችላት የእግዚአብሔር መንፈስና የእግዚአብሔር ቃል አላት፤ ዋናው ዓላማም በደለኛው የእግዚአብሔር ቃልና የእግዚአብሔር መንፈስ የሚለውን ሰምቶ በሁሉ እንዲወቀስና እንዲመከር በደለኝነቱን እንዲያምን በንስሐም ወደጌታ እንዲመለስ ማድረግ ነው እንጂ በደለኛውን መበቀል አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ በግልና በጋራ ተወቅሶ ወደ ቤተክርስቲያን የመጣውና ቤተክርስቲያንም የወቀሰችው ሰው የቤተክርስቲያንን መንፈሳዊ ወቀሳ ባይሰማስ?
4. እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ ይሁንልህ
ለዚህ የተሰጠው የጌታ መመሪያም፣ «ቤተክርስቲያንን ባይሰማት እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ ይሁንልህ» የሚል ነው፤ ተበዳዩ አማኝ ከዚህ አልፎ እንዲሄድ አልተፈቀደለትም፤ ንስሐ ሊገባ ባልቻለው በዚያ ሰው ላይ ቤተክርስቲያን በምትወስደው እርምጃ ላይም ግፊት ማድረግ አይኖርበትም፤ ወዳላመኑ ሰዎች ዘንድም ሄዶ «ንስሐ ባልገባው» በደለኛ ላይም ክስ ይመሥርት አልተባለም፤ ሆኖም እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ እንዲቆጥረውና እንዲተወዉ ታዟል፡፡ ሆኖም ቤተክርስቲያን በመቀጠል የምትወስደው እርምጃ አላት፡፡
በምድር የምታስሩት ሁሉ.. በምድር የምትፈቱት ሁሉ..
ቤተክርስቲያን ግን በአማኞች መካከል የሚነሱ በደሎችን እንድትዳኝ ሥልጣን የተሰጣት በመሆኗ በመቀጠል ስለምትወስደው እርምጃ ጌታ ሲናገር «በምድር የምታስሩት ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድር የምትፈቱት ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል» ሲል ተናገረ፤ ይህም ቤተክርስቲያን በአማኞች መካከል የሚነሡ ችግሮችን በበላይነት የመመልከት ሥልጣን እንዳላት የሚያመለክት ነው፤ ከዚህ አኳያም ማሰሩ በትክክል በዳዩን ሰው ከጉባኤ እንዲገለል ማድረግ ሲሆን መፍታቱ ደግሞ በተጸጸተ ጊዜ በዳዩን ሰው ይቅር ብሎ ወደ ኅብረት መቀበል ማለት ነው፡፡ ይህን የማድረግ ሥልጣንም በሥራ ላይ የሚውለው ሁለት ወይም ሦስት እንኳን በሚሆኑ አማኞች መካከል በሚገኘው ጌታ ኢየሱስ ነው፤ በምድር ላይ ንስሐ አንገባም በሚሉትና ልባቸውን በሚያደነድኑ፣ ወንድሞቻቸውንም በሚበድሉ በደለኞች ላይ ቤተክርስቲያን በምድር የምታስተላልፈው ውሳኔም በሰማይ በጌታ ዘንድ እውቅና አለው፤ በዚህ ዓይነት ቤተክርስቲያን በዳዮችን ከመካከሏ እንድታርቅ ሥልጣን ተሰጥቶአታል፡፡ ሐዋርያው ለቆሮንቶስ ሰዎች በቀዳሚ መልእክቱ በምዕራፍ 6 የተናገረለት ጉድለትም ቤተክርስቲያን ይህን በአማኞች መካከል የሚነሱ የግል በደሎችን በተሰጣት ሥልጣን መዳኘት አለመቻሏ እንደነበር ግልጥ ነው፡፡ ስለዚህም ሐዋርያው የሚከተለውን ለማለት ተገዶ ነበር፤ «ከእናንተ አንዱ ከባልንጀራው ሙግት ቢኖረው በቅዱሳን ፊት በመፋረድ ፋንታ በዓመፀኞች ፊት ሊፋረድ ይደፍራልን? ቅዱሳን በዓለም ላይ እንዲፈርዱ አታውቁምን? በዓለምስ ላይ ብትፈርዱ ከሁሉ ይልቅ ትንሽ ስለሚሆን ነገር ልትፈርዱ አትበቁምን? የትዳር ጉዳይ ይቅርና በመላእክት እንኳ እንድንፈርድ አታውቁምን? እንግዲህ ስለ ትዳር ጉዳይ የፍርድ ቤት ቢያስፈልጋችሁ በቤተክርስቲያን የተናቁትን ሰዎች ፈራጆች አድርጋችሁ ታስቀምጣላችሁን? አሳፍራችሁ ዘንድ ይህን እላለሁ፡፡ እንደዚህ ነውን? በወንድሞች መካከል ሽማግሌ ሊሆን የሚችል አንድ አስተዋይ ሰው በእናንተ ዘንድ አይገኝምን? ነገር ግን ወንድም ወንድሙን ይከሳል ይህም በማያምኑ ፊት ይደረጋልን? እንግዲህ ፈጽሞ የእርስ በእርስ ሙግት እንዳለባችሁ በእናንተ ጉድለት ነው፡፡ ብትበደሉ አይሻልምን? ብትታለሉስ አይሻልምን? ነገር ግን እናንተ ትበድላላችሁ ታታልሉማላችሁ ያውም ወንድሞቻችሁን» /ቊ.1-8/፡፡
የቆሮንቶስን አማኞች ጉድለት በመከተል የገዛ ወንድምን ወደማያምኑ ፈራጆች መጎተትና በዚህም የአማኞችን የከበረ ማንነት በዓለም ፊት የማስነወሩ ተግባር ሊወገድ የሚችለውም ቤተክርስቲያን ይህን ሥልጣን ስትጠቀም ነው፤ ቤተክርስቲያንም ከጌታ ያገኘችውን ውበት ጠብቃ መኖር የምትችለው በዚህ ሥልጣን ተጠቅማ ክፉዎችን ከመካከሏ ማራቅ ስትችል ነው፡፡ ምንም እንኳን ከአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ እስከዚህ ዘመን ድረስ ሰይጣን በአማኞች መካከል መለያየትን በመፍጠሩ ምክንያት በአንድ ስፍራ አማኞች እንደ ጌታ ፈቃድ ከመካከላቸው ያገለሉት በደለኛ በሌላው ስፍራ ባሉ አማኞች ነን ባዮች እንደ ሰማዕት ተቈጥሮ ተቀባይነት የሚያገኝበት ሁኔታ በእጅጉ የሚታይ ቢሆንም አሁንም ይህ ሥልጣን ሁለት ወይም ሦስት ሆነው በጌታ ስም በሚሰበሰቡ እውነተኛ አማኞች ዘንድ መኖሩ የሚያጠራጥር አይደለምና እውነተኛ አማኞች ይህን ሥልጣን ተጠቅመው ክፉን ከመካከላቸው እንዲያርቁ አለመግባባቶቻቸውንም ወደማያምኑት ከመውሰድ እንዲታቀቡ፣ በነውር የተገለሉትንም በደፈናው ወደኅብረታቸው ከመቀበልም እንዲጠበቁ ይመከራሉ፡፡
አማኞች ይህን ጌታ የሰጣቸውን ሥልጣን ተጠቅመው አንድን በደለኛ ከመካከላቸው ቢያስወግዱና ቆይቶ ኃጢአቱ የተያዘበት ሰውም ልቡ ተነክቶ ወደ ጌታ ኢየሱስና ወደ ቤተክርስቲያን በንስሐ ቢመለስ አማኞች ኃጢአቱ እንዲሰረይለት በመስማማት የሚጸልዩለት ጸሎት በጌታ ዘንድ ፍጹም ተሰሚነት አለውና ጌታም ይቅር ይለዋል፡፡ ያ ሰው አልመለስም በማለት ቢቀጥል ግን ይህ በደሉ በጌታ ዘንድ እንደተያዘበት ይኖራል፤ ይህም ማለት የጌታ የሆኑት በምድር ተሰብስበው እንደ ጌታ ልብ የሚወስኑት ውሳኔ በጌታ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሆኑን እንድናውቅ ያስረዳናል፤ ቤተክርስቲያንም በዚህ ዓይነት የማሰርና የመፍታት ሥልጣኗን ትተገብራለች፡፡
ሥልጣኑ የቤተክርስቲያን እንጂ የግለሰብ አይደለም
ሆኖም ይህ ሥልጣን አማኞች በኅብረት የተቀበሉት እንጂ በግለሰቦች እጅ የሚገኝ አይደለም፤ ምንባቡም እንደሚያመለክተው ጌታ ይህን ሥልጣን የሰጠው ሁለት ወይም ከዚያ የሚበልጥ ቊጥር ላላቸውና የሚሠሩትን በመስማማት ለሚያደርጉ የአማኞች ኅብረት ነው እንጂ ለአንድ ግለሰብ አይደለም፡፡ ስለሆነም በጥቅሉ በአማኞች መካከል በሚነሡ የግል አለመግባባቶችም ሆነ ሌሎች ጉዳዮችን የተመለከቱ የሥነሥርዓት ወይም የዲሲፕሊን እርምጃዎች ለግለሰብ የተሰጡ አይደሉም፡፡ በማቴ.16 ለጴጥሮስ እንደተባለለት የወንጌል መልእክተኞች በእግዚአብሔር ቃል መክፈቻነት ሰዎችን ያስራሉ ይፈታሉ፤ ይሁን እንጂ አንባቢው በማቴ.16 ስለማሰርና ስለመፍታት የተነገረው በማቴ.18 ከተነገረው ፈጽሞ የሚለይ መሆኑን ሊረዳ ይገባዋል፡፡ በማቴ.16 ላይ የተነገረው ማሰርና መፍታት ጌታ በራሱ አለትነት ላይ ወደሚገነባት ቤተክርስቲያኑ አማኞች ሕያዋን ድንጋዮች ሆነው እንዲገቡ ከሚያስችለውና በመክፈቻነቱ ከተገለጠው ከወንጌል ቃል ወይም ምስክርነት ጋር በተያያዘ መልኩ ሲሆን በማቴ.18 የተነገረው ማሰርና መፍታት ግን የተገለጠው ወንድማቸውን በሚበድሉ አማኞች ላይ ከሚወሰደው እርምጃ ጋር በተያያዘ መልኩ ነው፡፡
በማቴ.18 ላይ ለቤተክርስቲያን የተሰጣት ሥልጣን በአማኞች መካከል በሚነሡ ጉዳዮች ላይ ያተኰረ ቢሆንም ቤተክርስቲያን በዚሁ ሥልጣን ከዚህ ውጪም ባሉ ጉዳዮች ላይ ክፉን ከመካከሏ ማስወገድ የምትችል መሆኗን የሚገልጡ በርካታ ምንባቦች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ በቆሮንቶስ ዝሙት የፈጸመውን ሰው «ክፉን ከመካከላችሁ አውጡት» /1ቆሮ.5፡13/ በሚለው የተቀደሰ ሐሳብ እርሱን ከጉባኤ ማግለሉ ማሰር ሲሆን በተጸጸተ ጊዜ ደግሞ «ከልክ በሚበዛ ቅጣት እንዳይዋጥ ይልቅ ተመልሳችሁ ይቅር ማለትና ማጽናናት ይገባችኋል» /2ቆሮ.2፡7/ በሚለው ቃል መሠረት እርሱን በፍቅር መቀበል መፍታት ነው፡፡ ሐዋርያውም በዚያ ሰው ላይ እንዲህ ያለ እርምጃ እንዲወሰድበት ሐሳብ ሲያቀርብ «እናንተና መንፈሴም ከጌታችን ከኢየሱስ ኃይል ጋር ተሰብስበን» /1ቆሮ.5፡4/ ማለቱና «ይቅር የምትሉትን እኔ ደግሞ ይቅር እለዋለሁ» በማለት ከእነርሱ ጋር በመስማማት ይቅር ማለቱ /2ቆሮ.2፡9/ ከኃጢአትም ሆነ ከሌሎች የዲሲፕሊን እርምጃዎች ጋር የተያያዘ ለግለሰብ የተሰጠ መብትና ሥልጣን እንደሌለና ለዚህ ዓይነቱ ተግባርና ሥልጣንም ቤተክርስቲያን ብቸኛ ባለሥልጣንና የክርስቶስ እንደራሴ እንደሆነች ያሳያል፡፡ ስለሆነም ማቴ.18ን በተመለከተ ቤተክርስቲያን በሥነምግባር ጉድለት ኃጢአቱን የያዘችበት ሰው ኃጢአቱ የሚያዝበትም ሆነ ይቅር የሚባልለት አማኞች በጌታ ዙሪያ ተሰብስበው በሚስማሙበት ውሳኔ መሠረት እንጂ እንደምድራዊ አሠራር በክርስቶስ መንጋ ላይ ራሳቸውን ባለሥልጣናትና ገዢዎች ያደረጉ ግለሰቦች በሚወስዱት እርምጃ በኩል አይደለም፡፡ አማኞች ተስማምተው በደለኛውን በደለኛ እንደሆነ ወስነው ከማህበር ሲያገሉት ወይም የተገለለውን መጸጸቱን አይተው በፍቅር ሲቀበሉት ጌታ በውሳኔአቸው ይተባበራል፡፡ ቤተክርስቲያንም ውሳኔዋን ለጌታ በጸሎት ታስታውቃለች /ማቴ.18፡19/፡፡
የቤተክርስቲያንን ውሳኔ የሚያጸናውና ተግባራዊ የሚያደርገው «በሰማይና በምድር ሥልጣን ሁሉ» የተሰጠውና /ማቴ.28፡18/ በስሙ በሚሰበሰቡት መካከል የሚገኘው ጌታ ኢየሱስ ነው /ማቴ.18፡20/፡፡ ቤተክርስቲያን ለውሳኔዋ የሚያበቃትንም መለኮታዊ ድጋፍና አግባብነት ያለው ውሳኔ እንድትወስን የሚረዳትን ምሪት የምታገኘው ከእርሱ በመካከሏ ከሚገኘው ጌታ ብቻ ነው፤ በመካከሏ ለመገኘቱ ደግሞ መስፈርቱ በስሙ መሰብሰቧ ብቻ ነው፤ ከሁለት እስካልወረደ ድረስ የአማኞች ቊጥር ማነስም ቤተክርስቲያንን ይህን ሥልጣን ከመገልገል አያግዳትም፤ ሥልጣኑን የሚሰጣትም ያው ስትሰበሰብ በመካከሏ የሚገኘው ጌታ ኢየሱስ ብቻ ነው፡፡ የዚህ ሥልጣን አጠቃምም የተቀደሱ መነሻ ሐሳቦች አሉት፤ ይኸውም ጌታን ለማክበር፣ የጉባኤን ንጽህና ለመጠበቅና አጥፊዎችን አቅንቶ ገንዘብ ለማድረግ ሲባል ብቻ ነው፤ እነዚህን መርሆዎች ግብ ባላደረገ መልኩ ሥልጣኑን እንድንሠራበት ጌታ አይፈቅድልንም፡፡
የቤተክርስቲያንን ውሳኔ የሚያጸናውና ተግባራዊ የሚያደርገው «በሰማይና በምድር ሥልጣን ሁሉ» የተሰጠውና /ማቴ.28፡18/ በስሙ በሚሰበሰቡት መካከል የሚገኘው ጌታ ኢየሱስ ነው /ማቴ.18፡20/፡፡ ቤተክርስቲያን ለውሳኔዋ የሚያበቃትንም መለኮታዊ ድጋፍና አግባብነት ያለው ውሳኔ እንድትወስን የሚረዳትን ምሪት የምታገኘው ከእርሱ በመካከሏ ከሚገኘው ጌታ ብቻ ነው፤ በመካከሏ ለመገኘቱ ደግሞ መስፈርቱ በስሙ መሰብሰቧ ብቻ ነው፤ ከሁለት እስካልወረደ ድረስ የአማኞች ቊጥር ማነስም ቤተክርስቲያንን ይህን ሥልጣን ከመገልገል አያግዳትም፤ ሥልጣኑን የሚሰጣትም ያው ስትሰበሰብ በመካከሏ የሚገኘው ጌታ ኢየሱስ ብቻ ነው፡፡ የዚህ ሥልጣን አጠቃምም የተቀደሱ መነሻ ሐሳቦች አሉት፤ ይኸውም ጌታን ለማክበር፣ የጉባኤን ንጽህና ለመጠበቅና አጥፊዎችን አቅንቶ ገንዘብ ለማድረግ ሲባል ብቻ ነው፤ እነዚህን መርሆዎች ግብ ባላደረገ መልኩ ሥልጣኑን እንድንሠራበት ጌታ አይፈቅድልንም፡፡