በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት መኖር እንዴት እንደሚገባ ታውቅ ዘንድ እጽፍልሃለሁ፤ ቤቱም የእውነት ዓምድና መሠረት፥ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ነው።(1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 3:15)
1BIBLE
በመጀመሪያ እግዚአብሔር.........................................

የቤተክርስቲያን መሠረት

ቤተክርስቲያን የሚለው ቃል ትርጉሙ ምን እንደሆነ ከተመለከትን አሁን ደግሞ ቤተክርስቲያን የተመሠረተችበት መሠረት ምን እንደ ሆነ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እናያለን፡፡ ማንኛውንም መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት ከመሠረቱ ጀምረን ካላወቅን የሚኖረን መረዳት የተሟላ ካለመሆኑም በላይ ጣልቃ በሚገቡ የሰው ሐሳቦች ምክንያት በተሳሳተ መንገድ ልናስብም እንችላለን፡፡ እያንዳንዱ እውነተኛ አማኝ የቤተክርስቲያን አባል እንደመሆኑ መጠን ትክክለኛ ስፍራውን ያውቅ ዘንድ ይህንን ጽኑ የሆነ የቤተክርስቲያን መሠረት አጥብቆ ሊረዳ ይገባዋል፡፡ የሁላችንንም ትኵረት በእጅጉ የሚስበውን ይህንን የቤተክርስቲያን መሠረት የሚያሳውቀን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ የሚገኘው «ቤተክርስቲያን» የሚለው ቃል በአዲስ ኪዳን ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ተጽፎ በሚገኝበት በማቴ.16፡13-18 ውስጥ ነው፡፡ ይህም ክፍል እንደሚከተለው ይነበባል:-

«ኢየሱስም ወደ ፊልጶስ ቂሳርያ አገር በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን:- የሰውን ልጅ ማን እንደሆነ ይሉታል? ብሎ ጠየቀ፤ እነርሱም:- አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ ሌሎችም ኤልያስ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ አሉት፡፡ እርሱም:- እናንተስ እኔን ማን እንደሆንኩ ትላላችሁ? አላቸው፡፡ ስምዖን ጴጥሮስም:- መልሶ አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ አለ፡፡ ኢየሱስም መልሶ:- የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ፡፡ እኔም እልሃለሁ አንተ ጴጥሮስ ነህ በዚህችም ዓለት ላይ ቤተክርስቲያኔን እሠራለሁ የገሃነም ደጆችም አይችሏትም» ይላል፡፡

በዚህ ክፍል ውስጥ እንደተገለጠው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «... በዚህችም አለት ላይ ቤተክርስቲያኔን እሠራለሁ፤ የገሃነም ደጆችም አይችሏትም ...» ብሎ ሲናገር እንሰማዋለን/ቊ.18/፡፡ ጌታችን ይህንን ቃል የተናገረው የ3ቱን ዓመት የማስተማር ዘመኑን እያጠናቀቀ ሳለ ወደ ኢየሩሳሌም ለመጨረሻ ጊዜ ከመውጣቱ በፊት በፊልጶስ ቂሣርያ እያለ እንደነበር የዚህን ንባብ ምዕራፍ ስናጠና እንደርስበታለን/ቊ.21/፡፡ በዚያ ጊዜ ጌታ ኢየሱስ «ቤተክርስቲያኔን እሠራለሁ» ብሎ በትንቢታዊ ቃል መናገሩ በጊዜው ገና ቤተክርስቲያን ተሠርታ እንዳልነበረ ያመለክተናል፡፡ በእርግጥም በደሙ በሚደረግ ቤዛነት ሕዝብን ከነገድ ከቋንቋ ሳይዋጅ ቤተክርስቲያን ልትሠራ እንዴት ትችላላች? ቤተክርስቲያንን በገዛ ደሙ እንደዋጃት የሚያስረዳ ግልጽ ንባብ እናገኛለንና/የሐ.ሥ.20፡28/፡፡ ስለዚህ በክርስቶስ ሞት የኃጢአት ዕዳ ከመከፈሉ በፊት ቤተክርስቲያን እንዳልተሠራች ልንገነዘብ እንችላለን፡፡

አሁን ደግሞ የቤተክርስቲያንን መሠረት በተመለከተ «...በዚህችም አለት ላይ ቤተክርስቲያኔን እሠራለሁ የገሃነም ደጆችም አይችሏትም...» ብሎ ጌታችን በተናገረው ቃል ውስጥ ያሉትን ሁለት ዋና ዋና ኃይለ ቃላትን እንመልከት፡፡

1. በዚህችም ዓለት ላይ

ጌታ ኢየሱስ ቤተክርስቲያኑን የሚሠራበትን መሠረት ሲገልጥ «በዚህችም ዓለት ላይ ቤተክርስቲያንን እሠራለሁ» ብሏል፡፡ ከዚህም ቃል የቤተክርስቲያን መሠረት «ዓለት» እንደሆነ እንረዳለን፡፡ በማቴ7፡24-27 የተመዘገበውን የጌታችንን ምሳሌ ስናነብ ልባም ሰው ቤቱን በዓለት ላይ እንደሚሠራና ያንንም በዓለት ላይ የተመሠረተ ቤት ዝናብ ቢወርድም ጐርፍ ቢመጣም ነፋስ ቢነፍስም ፈጽሞ ሊወድቅ እንደማይችል ያስረዳል፡፡ በተቃራኒው ግን ሰነፍ ሰው የሚሠራው በአሸዋ ላይ የተመሠረተ ቤት ዝናብ ሲወርድ ጐርፍ ሲመጣ ነፋስም ሲነፍስ ታላቅ አወዳደቅ እንደሚወድቅ ይገልጻል፡፡ ከዚህ አንፃር ስንመለከተው ኢየሱስ ክርስቶስ ቤቱን በዓለት ላይ የሠራ «ልባም ሰው» ነው፡፡

«በዚህችም ዓለት ላይ...» የሚለውን ይህንን ቃል የሚያነቡ ሁሉ «ይህች ዓለት ምንድር ናት?» ብለው መጠየቃቸው የማይቀር ነው፡፡ ጌታችን ከዚህ ንባብ ቀደም ብሎ «አንተ ጴጥሮስ ነህ» ካለ በኋላ «በዚህችም ዓለት ላይ ቤተክርስቲያኔን እሠራለሁ» ብሎ መናገሩን በመመልከት በዚህ ንባብ ውስጥ ዓለት የተባለው «ጴጥሮስ ነው» የሚል የተሳሳተ መረዳት መኖሩ ይታወቃል፡፡ ይህም መረዳት ንባቡ የቀረበበትን ሰዋስው በተለይም የቃሉን ጾታ ካለማስተዋል የመጣ ነው፡፡ ጌታችን «አንተ ጴጥሮስ ነህ» የሚለውን ቃል የተናገረው በተባዕታይ ጾታ እንደሆነ ያስተዋለ አንባቢ «በዚህችም ዓለት» የሚለውን ቃል ሲያነብ ዓለቷ ጴጥሮስ ነው ማለት አይችልም፤ ይህ የተባዕታይንና የእንስታይን ጾታ ማደባለቅ ነው፡፡ በዚህ ፈንታ ግን ጌታችን «በዚህች» በሚለው ጠቋሚ ቃል በእንስታይ ጾታ የጠራት ዓለት ምንድናት? ብሎ በመጠየቅ ምላሹን ከዚሁ ንባብ ውስጥ ያፈላልጋል፡፡ በሰው ሐሳብ ሳይጠላለፍ በመንፈስ ቅዱስ በተቃኘ ኅሊና ሆኖ እሰካነበበ ድረስም ምላሹን በዚሁ አንቀጽ ውስጥ በቅርቡ ያገኛል፡፡ «በዚህች» በሚለው የቅርብ አመልካች ቃል የተጠቆመችው የዚህች ዓለት ምንነት ኢየሱስ ቃሉን በሚናገርበት በዚያው ሰዓት የተገለጠ መሆን አለበት፡፡ ስለዚህም አንባቢው ዓይኖቹን ከፍ አድርጐ ወደ ቊጥር 16 ቢመለከት ጌታችን ስለማንነቱ ለደቀመዛሙርቱ ላቀረበው ጥያቄ ጴጥሮስ የመለሳትን አጭርና ግልጽ መልስ ያገኛል፡፡ እርስዋም «አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ» ብሎ በሥጋና በደም ሳይሆን በሰማያዊ መገለጥ የተናገራት ቃል ናት፡፡

በግሪክ ቋንቋ በዚህ ጥቅስ ውስጥ ጴጥሮስ የሚለው ቃል «petros/ፔትሮስ/» ተብሎ የተጻፈ ሲሆን ዓለት የሚለው ቃል ግን «petra/ፔትራ/» ተብሎ ተጽፏል፤ ይህም በሁለቱ ቃላት መካከል ግልጽ የሆነ የትርጉም ልዩነት እንዳለ ያሳያል፤ «ፔትሮስ» ማለት ከዓለት የተከፈለ ድንጋይ /ጡብ/ ማለት ሲሆን «ፔትራ» ማለት ራሱ ሙሉው ዓለት ነው፡፡ ጌታችንም ቤተክርስቲያኔን በፔትራ /በንጥፍ ዓለት/ ላይ እመሠርታለሁ አለ እንጂ በፔትሮስ /በጡብ/ ላይ እመሠርታለሁ አላለም፤ ስለሆነም የቤተክርስቲያን መሠረት «አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ» የምትለው የእምነት ቃል ናት እንጂ ጴጥሮስ አለመሆኑን አንባቢው ሊያስተውል ይገባል፡፡ ይህችም የእምነት ቃል ስለክርስቶስ የምትናገር ስለሆነ የቤተክርስቲያን መሠረት ራሱ ክርስቶስ ነው ቢባል ትክክል ነው፡፡ በ1ቆሮ.3፡11 ላይ ‹ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልምና፤ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው› ተብሎ ተጽፏልና፡፡

የቤተክርስቲያን መሠረት «አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ» የምትለው የእምነት ቃል ናት እንጂ ጴጥሮስ አለመሆኑን አንባቢው ሊያስተውል ይገባል፡፡

ይህንን ቃል የሕይወት መመሪያ ያደረገ ክርስቲያን እኔ የምሰበሰብበት መንፈሳዊ ጉባዔ የተመሠረተው በምን ላይ ነው? ብሎ በማስተዋል ሊመረምር ይገባዋል፡፡ በዘመናችን በየስፍራው የሚቋቋሙት ድርጅታዊ ገጽታ ያላቸው አብያተክርስቲያናት የቆሙበትን መሠረት በጥንቃቄ ልንመረምር ያስፈልጋል፡፡ ለቤተክርስቲያን ህልውና መሠረት የሆነውን «ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነው» የሚለውን የእምነት ቃል ወደ ጐን በመተው ወይም ትኩረት በመንፈግ፣ መሠረት ተደርገው ያልተነገሩትን ሌሎች መንፈሳውያን ትምህርቶችና ሥርዓቶች መሠረት ማድረግ አሳዛኙ የክርስቲያኖች ገጽታ እየሆነ መጥቷል፤ ከ4ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የሚታየውን የዓለማዊቷን ቤተክርስቲያን መለያየት ስንመለከት ዋነኛ ምክንያቱ ሥልጣንን፣ ጥቅምን፣ ክብርንና ማዕርግን ማስጠበቅ ቢሆንም ሰበብ የሆኑት መንፈሳዊ ምክንያቶች ግን፣ ክርስቶስ አንድ ባሕርይ ወይስ ሁለት ባሕርይ ነው?፣ ጥምቀተ ህፃናት ልክ ነው ወይስ አይደለም? ሥዕል ያስፈልጋል ወይስ አያስፈልግም? በጌታ እራት ጊዜ ኅብስቱና ወይኑ ወደ ሥጋና ደም ይለወጣል ወይስ አይለወጥም? የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ሲገለጡ እንዴት ነው? በልሳን መናገርና አጠቃቀሙን የምንረዳው እንዴት ነው? የቤተክርስቲያን አስተዳደር በሽማግሌዎች ወይስ በካህናት ይሁን? የሚሉትና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ «ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው» የሚለውን የቤተክርስቲያን መሠረት የማይተኩ ናቸው፡፡ በእነዚህ አርእስተ ጉዳዮች ያሉት እውነተኛ ትምህርቶችም ቢሆኑ ለቤተክርስቲያን እንደ ዋና መሠረት ታይተው ጉባዔ የሚመሠረትባቸው ቤተክርስቲያን የሚከፈልባቸው አዲስ ስም የሚወጣባቸው ምክንያቶች መሆናቸው አሳዛኝ ነው፡፡ ይሁንና ከዚህ አስተሳሰብ ተለይተው መሠረታቸውን በጥልቀት የተመለከቱ በሁሉም ስፍራ የሚገኙት የእውነተኛ ክርስትና ቅሬታዎች ግን ራሳቸውን «ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነው» በሚለው መሠረት ላይ ያገኙታል!!

 

2. የገሃነም ደጆች አይችሏትም

ልባም ሰው የሠራውንና በጽኑ ዓለት ላይ የተመሠረተን ቤት ዝናብ ወርዶ፣ ጐርፍ ጐርፎ፣ ነፋስ ነፍሶ ቢገፋውም ሊወድቅ እንደማይችል የተረጋገጠ ነው /ማቴ7፡24-25/፡፡ ዝናብ፣ ጐርፍና ነፋስ በክርስቲያኖች ላይ ስለ ወንጌል የሚደርስ ነቀፋን፣ ስደትንና የተለያየ መከራን እንዲሁም የስህተት ትምህርትን ሊያመለክቱ ይችላሉ፡፡ እነዚህም በጽኑ መሠረት በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የተመሠረተችውን የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን ቢገፏትም ሊጥሏት አይችሉም፡፡ ቤተክርስቲያንን በተመለከተ «የገሃነም ደጆች አይችሏትም» የሚል ጽኑ ቃል ከቤተክርስቲያን መሥራች ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ስንሰማ ልባችን በድል ስሜት ይሞላል፡፡

«የገሃነም ደጆችም አይችሏትም» በሚለው ባማርኛው ንባብ ውስጥ «ገሃነም» የሚለው ቃል በሌሎች ቋንቋዎች «ሲኦል» ተብሎ የተተረጐመው ቃል ነው፡፡ አዲስ ኪዳን በተጻፈበት በግሪኩ ቋንቋም ሆነ በእንግሊዝኛው፣ እንዲሁም በግእዙ ሲኦል ተብሎአል፡፡ «ሲኦል» የሚለው ቃል ከሞት ጋር የተያያዘ ትርጉም እንዳለው ግልጽ ነው/1ቆሮ15፡55/፤ ማለትም ሲኦል ኃጢአተኛ የሞት ፍርድን የሚቀበልበት የሥቃይ ስፍራ ነው/ሉቃ.16፡23/፡፡ ስለዚህ ዋነኞቹ የሲኦል ደጆች ሞትና መውጊያው ናቸው ቢባል ትክክል ነው፡፡ የሞትም መውጊያ ኃጢአት እንደሆነ ተጽፏል/1ቆሮ15፡56/፡፡ ቤተክርስቲያንን ግን እነዚህ የገሃነም ደጆች የሆኑት ኃጢአትና ሞት እንደማይችሏት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አረጋግጦ ተናገረ፡፡ የዚህም ምክንያቱ ቤተክርስቲያን የተመሠረተችበት ዓለት ማለትም «ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነው» የሚለው እውነት ጽኑዕ ስለሆነ ነው፤ ይልቁንም ኢየሱስን የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነው ብለው የሚያምኑ ክርስቲያኖች ሞትና መውጊያውን ሊፈሩት አይችሉም፤ ኢየሱስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ መሆኑን በመስቀል ላይ በሞተ በ3ኛው ቀን ከሞት በመነሣት በተግባር አረጋግጧልና/ሮሜ1፡4/፤ መላእክትም «ሕያውን ከሙታን መካከል ስለምን ትፈልጉታላችሁ?» ብለው በማለዳ ወደ ኢየሱስ መቃብር መጥተው ለነበሩ ሴቶች ተናግረዋል/ሉቃ.24፡5/፤ ሴቶቹም «ሕያው ነው የሚሉ የመላእክትን ራእይ አየን» እያሉ መስክረዋል/ሉቃ.24፡23/፤ ጌታችንም በብዙ ማስረጃ ከሕማማቱ በኋላ ሕያው ሆኖ ለደቀመዛሙርቱ ራሱን አሳይቷቸዋል/የሐ.ሥ.1፡3/፡፡ ጴጥሮስም በመልእክቱ ውስጥ ሲጽፍ «በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ» በማለት ይናገራል/1ጴጥ.3፡18/፡፡ ኢየሱስ የሕይወት ምንጭ ስለሆነና ዘላለማዊ ሕይወት ያለው የአብ ልጅ በመሆኑ በዚህ የሕይወት ኃይል ከሙታን ተነሥቷል፡፡ ያ በአብ ያለው ሕይወት በእርሱም ነበር /ዮሐ1፡4/፤ ይህም ሕይወት መለኮታዊ ሕይወት ነው፤ ስለዚህ ፍጻሜ የሌለው ሕይወት ብቻ ሳይሆን ጅማሬም የሌለው ሕይወት ነው፡፡ በአባቱ ያለው ያ ሕይወት የእርሱም ሕይወት የሆነለት ይህ ልጅ /ኢየሱስ/ ለእኛም የሰጠን ሕይወት ያንኑ በአብ ዘንድ ያለውን መለኮታዊ ሕይወት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን ሲያስረዳ «ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል እንመሰክርማለን፤ ከአብ ዘንድ የነበረውን ለእኛም የተገለጠውን የዘላለምን ሕይወት እናወራላችኋለን» ይላል /1ዮሐ.1፡2/፡፡ የእግዚአብሔር ቃል እንደሚነግረንም ሰዎች እርሱን ባመኑ ጊዜ ኢየሱስ ራሱ ወደ እነርሱ ይገባል /ራእ.3፡20/፤ ኢየሱስ ወደ ልባቸውና ወደ ኑሮአቸው የገባ አማኞችም የመለኮታዊ ሕይወት ባለቤት ይሆናሉ፤ በሌላ አነጋገር የሚያገኙት የዘላለም ሕይወት ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ማለት ነው፤ «እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው» ተብሎ እንደተጻፈ /1ዮሐ.5፡20/፡፡

የሞትና የሲኦል መክፈቻ እንዳለው ገልጦ የነገረን ክርስቶስ /ራእ.1፡18/ «የገሃነም/የሲኦል/ ደጆች አይችሏትም» እያለ ቤተክርስቲያንን በተመለከተ የተናገረው ይህ እርግጠኛ ቃል ዲያብሎስ በዙሪያችን ለሚያሰማን የመከራና የሞት ድምፅ ጆሮ እንዳንሰጠው ያደርገናል፡፡ የክርስቶስ ኢየሱስ በመሆናችን ክርስቶስን ከበር ውጪ አውጥታ የሰቀለችውና ታሪኩንም በሞትና በመቃብር ለመደምደም ሙከራ አድርጋ የነበረችው ዓለም ብትጠላንም ሆነ ብታሳድደን እስከሞት ድረስ ታማኞች እንድንሆን የሚያጠነክር አስተማማኝ ዋስትና ከኢየሱስ አግኝተናል፡፡ ድንጉጥና ፈሪ የሆነው ልባችን ከዓለም የሚደርስብንን ነቀፋ ገና ሲሰማ የሞት ፍርሃት ሊያውከው ቢሞክርም «የገሃነም ደጆች አይችሏትም» የሚለውን ድምፅ ባስታወሰ ጊዜ የሞት ፍርሃቱ ሁሉ ከላዩ ይገፈፋል፡፡ ኢየሱስ ሰው የመሆኑ ዓላማ ይህ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ሲገልጥ «እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር ይኸውም ዲያብሎስ ነው በሕይወታቸውም ሁሉ ስለሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ» ይላል /ዕብ.2፡14/፡፡

ስለሆነም ሰይጣን እኛን ሊያስፈራራበት የሚችለው ትልቁ መሣሪያው ሞትና መውጊያው በኢየሱስ የተሰበረ መሆኑን ከልብ በማመን ከሞት ፍርሃት ነጻ ልንሆን ያስፈልጋል፡፡ በእርግጥ መሠረቷ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ በሆነላት አንዲቷ ቤተክርስቲያን ውስጥ አባል እንደሆኑ እርግጠኛ የሆኑ አማኞች «በዚህችም አለት ላይ ቤተክርስቲያኔን እሠራለሁ የገሃነም ደጆችም አይችሏትም» በሚለው የጌታችን የማረጋገጫ ቃል ስለሚያምኑ በዘመናቸው ሁሉ በሞት ፍርሃት ሊታሠሩ አይችሉም፡፡ ሞት ይይዘው ዘንድ ያልቻለው /የሐ.ሥ.2፡24/ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ በደሙ የዋጃትና ራስ የሆነላት ይቺ የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን የሲኦል ደጆች የሆኑት ሞትና መውጊያው እንዴት አድርገው ሊያናውጧት ይችላሉ? በእርግጥ ፈጽሞ አይችሉም፡፡

ስለዚህ ዛሬ ቤተክርስቲያን ልቧን አስፍታ ድምጿን ከፍ አድርጋ፡-

«ሞት ሆይ መውጊያህ የት አለ፤ ሲኦል ሆይ ድል መንሣትህ የታለ፤ የሞት መውጊያ ኃጢአት ነው፤ የኃጢአት ኃይል ሕግ ነው፤ ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ድል መንሣትን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን» /1ቆሮ.15፡55-57/ ብላ መዘመር ትችላለች፡፡www.ewnet.org.et/btm_files/aclesia.htm


 
ከእርሱም የሰማናት ለእናንተም የምናወራላችሁ መልእክት። እግዚአብሔር ብርሃን ነው ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም የምትል ይህች ናት።(1ኛ የዮሐንስ መልእክት 1:5)
This website was created for free with Own-Free-Website.com. Would you also like to have your own website?
Sign up for free