2. መዳን በሥራ ካልሆነ ለመልካም ሥራ ከጌታ የምናገኘው ምንድነው?
በእምነት መዳንን ካገኘን ወይም በክርስቶስ አዲስ ፍጥረት ከሆንን በኋላ የምንሠራው መልካም ሥራ ይኖራል፡፡ ይህንን በተመለከተም «እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን» ተብሎ ተነግሮናል/ኤፌ.2፡10/፡፡ ለዚህም መልካም ሥራችን ወደፊት በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት እንደየሥራችን በብድራት የሚከፈለን ዋጋ አለ፡፡ ይህም «መልካምም ቢሆን ክፉ እንዳደረገ በሥጋው የተሠራውን በብድራት ይቀበል ዘንድ ሁላችን በክርስቶስ በፍርድ ወንበር ፊት ልንገለጥ ይገባናልና» ተብሎ ተገልጿል /2ቆሮ.5፡10/፡፡ በሌላም ስፍራ «ሁላችን በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት እንቆማለንና» ይላል/ሮሜ14፡10/፡፡ በእነዚህ ንባቦች ውስጥ «ሁላችን» የሚለው ቃል ጸሐፊው ጳውሎስ ራሱን ጨምሮ መናገሩን ያሳያል፤ ጳውሎስ የዳነ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስን የሚቀበሉ ሁሉ የሚስማሙበት ጉዳይ ነው፤ ስለዚህ ጳውሎስን ጨምሮ ሁላችን የምንቀርብበት ይህ የክርስቶስ የፍርድ ወንበር የመዳን ያለመዳን ጉዳይ ገና የሚረጋገጥበት ዙፋን ሳይሆን የዳኑ ሰዎች በሥጋ ዘመናቸው ለሠሩት ሥራ ተገቢው የጽድቅ ብድራት የሚከፈልበት የፍርድ ወንበር ነው፡፡ ስለዚህ በመልካም ሥራችን የምናገኘው መዳንን ሳይሆን እንደየሥራችን የሆነ ብድራት ወይም ዋጋ ነው፡፡ ይህም «የማይጠፋ አክሊል» መሆኑ የተገለጸ ሲሆን/1ቆሮ9፡15/፣ በ2ጢሞ.4፡8 ላይ «የጽድቅ አክሊል»፣ በያዕ.1፡12፤ ራእ2፡10 ላይ «የሕይወት አክሊል»፣ በ1ጴጥ.5፡4 ላይ «የክብር አክሊል» ተብሎ ተጠርቷል፡፡
3. ያዕ.2፡14‐26 ባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የአብርሃምንና የረዓብን እምነትና ሥራ በማስረጃነት በመጥቀስ «ሰው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራ እንዲጸድቅ ታያላችሁ» ይላል/ቊ.24/፡፡ ይህ ቃል ቀደም ሲል ከተመለከትናቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እና በተለይ ደግሞ በሮሜ 4 ላይ ከተሰጠው ትምህርት አንጻር እንዴት ይታያል? ቢብራራ፡፡
መልስ
ሰው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራም እንደሚጸድቅ በያዕ.2 ውስጥ መገለጹ ሰው በእግዚአብሔር ዘንድ ስለመጽደቁ ሳይሆን አንድ ሰው መጽደቁ በሰው ዘንድ ስለመታየቱ ወይም ስለመረጋገጡ የሚገልጽ ነው፡፡ ቀደም ሲል በተመለከትናቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች መሠረት ሰው የሚድነው ወይም የሚጸድቀው በእምነት እንጂ በሥራ እንዳልሆነ እርግጥ ነው፤ ይህ በእምነት የመጽደቅ ጉዳይም በሰው ዘንድ ሳይሆን በእግዚአብሔር ዘንድ የሚታየው ነው፡፡
በሮሜ 4፡1‐8 የምናገኘው የእግዚአብሔር ቃል ይህን የሚያረጋግጥ ነው፤ በቊ.1 ላይ «በሥጋ አባታችን የሆነ አብርሃም ምን አገኘ እንላለን? አብርሃም በሥራ ጸድቆ ቢሆን የሚመካበት አለውና፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ዘንድ አይደለም» ይላል፤ «በእግዚአብሔር ዘንድ አይደለም» የሚለው ይህ ቃል በእግዚአብሔር ዘንድ በሥራ መጽደቅ እንደሌለ የሚገልጽ ነው፡፡ በዚህ ክፍል ሰው ያለ ሥራ በእምነት እንደሚጸድቅ ለማሳየት ሁለት ሰዎች በምሳሌነት ተጠቅሰዋል፤ እነርሱም አብርሃምና ዳዊት ናቸው፡፡ እነዚህ ሁለት ሰዎች በአንድነት መጠቀሳቸው በመጽሐፍ ቅዱስ የተለመደ ሲሆን /ማቴ.1፡1፤ የሐ.ሥ.13፡26‐36/ ይህንንም ታላቅ ርእሰ ጉዳይ ለማብራራት አብረው መጠቀሳቸው ወሳኝ ነው፡፡ አብርሃም የነበረው ሕግ ከመሰጠቱ በፊት ሲሆን ዳዊት ደግሞ በሕጉ ዘመን የነበረ ሰው ነው፤ ከሁለቱም ሰዎች አንጻር ሲታይ ግን በእግዚአብሔር ዘንድ ጽድቅ የሚቈጠረው በሥራ ሳይሆን በእምነት እንደሆነ ተብራርቷል፡፡
በቊ.3 ላይ አብርሃምን በተመለከተ ሲገልጽ «መጽሐፍስ ምን አለ? አብርሃም እግዚአብሔርን አመነ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት፤ ለሚሠራ ደመወዝ እንደ ዕዳ ነው እንጂ እንደ ጸጋ አይቈጠርለትም፤ ነገር ግን ለማይሠራ ኃጢአተኛውን በሚያጸድቅ ለሚያምን ሰውእምነቱ ጽድቅ ሆኖ ይቈጠርለታል» ይላል፡፡ በዚህም ቃል ውስጥ አብርሃም ጽድቅን ያገኘው እግዚአብሔርን ስላመነ ተቈጥሮለት እንጂ ጽድቅ ሠርቶ እንዳልሆነ እንገነዘባለን፡፡ ይህም ለሚያምን ሰው ሁሉ እግዚአብሔር የሚያደርገው መሆኑ ተገልጿል፡፡ በመቀጠል ደግሞ ዳዊት ይህን ጉዳይ በተመለከተ የተናገረው ተጠቅሷል፡፡ ይኸውም «እንደዚህም ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ሥራ ጽድቅን ስለሚቈጥርለት ሰው ብፅዕና ይናገራል እንዲህ ሲል፤ ‘ዓመፃቸው የተሰረየላቸው ኃጢአታቸውም የተከደነላቸው ብፁዓን ናቸው፤ ጌታ ኃጢአቱን የማይቈጥርበት ሰው ብፁዕ ነው’»/ቊ.6‐8/፤ በአብርሃም ሕይወት እንዳየነው እግዚአብሔር ሊቈጠርልን የማይገባውን ጽድቅ በእምነት ሲቈጥርልን እናያለን፤ በዚህ ዳዊት በተናገረው ቃል ውስጥ ደግሞ እግዚአብሔር ሊቈጥርብን የሚገባውን ኃጢአት ባለመቊጠር ጸጋውን ሲያሳይ እንመለከታለን፡፡ ይህም «እግዚአብሔር ያለ ሥራ ጽድቅን ስለሚቈጥርለት ሰው ብፅዕና» የተነገረ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ስለዚህ በሮሜ 4 ውስጥ የተሰጠው ትምህርት ሰው በእግዚአብሔር ዘንድ የሚጸድቀው ያለ ሥራ በእምነት መሆኑን የሚያሳይ ነው፤ ይህ እምነት በሥራ ሊገለጥ የሚችል እውነተኛ መሆኑን እግዚአብሔር ማወቅ ይችላልና፡፡
በያዕ.2 ውስጥ የምናገኘው ትምህርት ግን ጽድቅ ወይም መዳን በሰው ዘንድ የሚታየው ወይም የሚረጋገጠው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራም እንደሆነ የሚገልጽ ነው፡፡ በሰው ዘንድ የአንድ ሰው እምነት እውነተኛ እምነት መሆኑ ሊታይ የሚችለው በሥራ ነው፤ በቊ.14 ላይ «ወንድሞች ሆይ እምነት አለኝ የሚል ሥራ ግን የሌለው ሰው ቢኖር ምን ይጠቅመዋል፤ እምነቱስ ሊያድነው ይችላልን?» በማለት ያዕቆብ ጥያቄ ያነሳል፤ እዚህ ላይ «እምነት አለኝ» የሚለው ያ ሰው ራሱ ነው፡፡ እግዚአብሔር ይህ እምነት እውነተኛ መሆን አለመሆኑን በራሱ አምላካዊ እውቀት ያውቃል፤ ሰው ግን ይህን የሚያውቀው ሥራውን አይቶ ነው፤ እዚህ ላይ የተጠቀሰው «እምነት አለኝ» ባዩ ሰው ደግሞ ሥራ እንደሌለው ታውቋል፤ ስለዚህ በቊ.17 ላይ «ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው» ተብሏል፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ እውነተኛ እንደሆነ የሚታወቅ እምነት ግን ሥራ የሌለው ሊሆን አይችልም፤ በጊዜው ባይገለጥ እንኳ እግዚአብሔር ጽድቅ አድርጎ የቈጠረው እምነት ከሆነ በሥራ መገለጡ አይቀርም፡፡ ያን ጊዜም በሰው ዘንድ ይታያል፤ ስለዚህ በቊ.18 ላይ እንደተጠቀሰው «አንድ ሰው አንተ እምነት አለህ እኔም ሥራ አለኝ እምነትህን ከሥራህ ለይተህ አሳየኝ እኔም እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ ይላል» ተብሎ በሁለት ሰዎች መካከል በዚህ ጉዳይ ሊባል የሚችለው ነገር ተነግሮናል፤ እነዚህ ሁለት ሰዎች አንዱ እምነት አለኝ የሚለው ሰው ሲሆን ሌላው ደግሞ ሥራ ያለውና እምነቱን በሥራው ማሳየት የሚችለው ሰው ነው፤ እየተናገረ ያለውም ይህ እምነቱን በሥራው ማሳየት የሚችለው ሰው ነው፡፡ «እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ» በሚለው አገላለጽም ሥራ እውነተኛ እምነት በሰው ዘንድ /ፊት/ የሚገለጥበት ማሳያ መሆኑን እንረዳለን፤ ይህ እምነቱን በሥራው ማሳየት የሚችለው ሰው ሥራ የሌለው እምነት ያለውን ሰው እንዲህ እያለ ይወቅሰዋል፤ «እግዚአብሔር አንድ እንደሆነ አንተ ታምናለህ መልካም ታደርጋለህ፤ አጋንንት ደግሞ ያምናሉ ይንቀጠቀጡማል፡፡» ይለዋል /ቊ.19/፡፡ በዚህ ቃል ውስጥ ሥራ የሌለው እምነት ያለው ሰው እምነቱ የተነጻጸረው ከአጋንንት እምነት ጋር መሆኑ ሰውየው የዳነ ሰው እንዳልሆነ ያሳያል፤ ምክንያቱም መዳን በእምነት ነው ሲባል በእውነተኛ እምነት እንጂ እንደ አጋንንት እምነት ባለ በዚህ ዓይነት እምነት አይደለም፡፡
በመቀጠልም ለዚህ አፍኣዊ እምነት ላለው ሰው የአብርሃም እምነትና ሥራ በማስረጃነት ቀርቦለታል፤ «አንተ ከንቱ ሰው እምነት ከሥራ ተለይቶ የሞተ መሆኑን ልታውቅ ትወዳለህን? አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን በመሠዊያው ባቀረበ ጊዜ በሥራ የጸደቀ አልነበረምን? እምነት ከሥራው ጋር አብሮ ያደርግ እንደነበረ በሥራም እምነት እንደተፈጸመ ትመለከታለህን? መጽሐፍም አብርሃም እግዚአብሔርን አመነ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት ያለው ተፈጸመ፤ የእግዚአብሔርም ወዳጅ ተባለ፡፡» ይላል /ቊ.20‐23/፡፡ በዚህ ክፍል አብርሃም ልጁን በመሠዊያው ላይ ማቅረቡ የአብርሃም ሥራ ሆኖ ቀርቧል፤ በዚህም ሥራ የአብርሃም እምነት እንደተፈጸመ ወይም ፍጹም እንደተደረገ/ቊ.22 አ.መ.ት. ተመልከት/ ተገልጧል፤ ከዘፍ.15፡4‐6 እንደምንረዳው ደግሞ «አብርሃም በእግዚአብሔር አመነ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት» የተባለው እግዚአብሔር ለአብርሃም ከጉልበቱ የሚወጣው እንደሚወርሰው በተናገረውና የሰማይ ከዋክብትን አሳይቶ «ዘርህም እንደዚሁ ይሆናል» ባለው ጊዜ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ይስሐቅን በመሠዊያ ላይ እስከሚያቀርብበት ጊዜ ድረስ ብዙ ዓመታት ተቈጥረዋል፤ በ86 ዓመቱ እስማኤልን ወልዷል/ዘፍ.16፡16/፤ ከ13 ዓመታት በኋላ በ99 ዓመቱ ራሱ አብርሃምና ልጁ እስማኤልም ተገርዘዋል/ዘፍ17፡24‐25/፤ በ100 ዓመቱ ይስሐቅን ወልዷል/ዘፍ.21፡5/፤ ከዚያም በፍልስጥኤም ምድር ብዙ ቀን እንግዳ ሆኖ ተቀምጧል/ዘፍ.21፡34/፤ እንግዲህ ልጁ ይስሐቅን በመሠዊያ ላይ ያቀረበው ከዚህ ሁሉ በኋላ ይስሐቅ ካደገ በኋላ እንደሆነ እንረዳለን፤ በዚህ ጊዜ አብርሃም በሥራም እንደጸደቀ ተነግሮናል፤ አብርሃም በእግዚአብሔር ዘንድ የጸደቀው ግን «ከጉልበትህ የሚወጣው ይወርስሃል»፣ ዘርህ እንደዚሁ ይሆናል» የሚለው የተስፋ ቃል በተሰጠው ጊዜ ማለትም ይስሐቅ ገና ባልነበረበት ጊዜ ነው/ሮሜ4፡18 ተመልከት/፡፡ ያን ጊዜ በእግዚአብሔር ስላመነ ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት፡፡ ከብዙ ዓመታት በኋላ ደግሞ ልጁን ይስሐቅን በመሠዊያው ባቀረበ ጊዜ በሥራም ጸደቀ፤ ይህም ማለት በሰው ዘንድ ታየ ተረጋገጠ ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን ለአብርሃም ጽድቅን ለመቊጠር ልጁ ይስሐቅን በመሠዊያ ላይ እስኪያቀርብ ድረስ መጠበቅ አላስፈለገውም፤ አብርሃም ባመነ ጊዜ እምነቱን ጽድቅ አድርጎ ቈጥሮለታል፡፡
አብርሃም የተገረዘው እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ከተቈጠረለት ከ13 ዓመታት በኋላ በመሆኑ መገረዙም ቢሆን በእግዚአብሔር ዘንድ ለመጽደቁ ምክንያት አልነበረም/ሮሜ4፡9‐12/፤ ነገር ግን ይህ መገረዙ «ሳይገረዝ በነበረው እምነት ያገኘው የጽድቅ ማኅተም» የሆነ ምልክት/ማረጋገጫ/ ነበር/ሮሜ4፡11/፡፡ እንዲሁም ሕግ የተሰጠው ከ430 ዓመታት በኋላ በሙሴ ጊዜ በመሆኑ አብርሃም በዘመኑ በሕግ ሥራ ሊጸድቅ አይችልም፡፡ ስለዚህ አብርሃም የጸደቀው በሕግ ሥራ ሳይሆን በእምነት ነበር፡፡ ዛሬም ቢሆን ሰው የሚጸድቀው በሥራ ሳይሆን በእምነት እንደሆነ ለማወቅ «ለማይሠራ ኃጢአተኛውን በሚያጸድቅ ለሚያምን ሰው» እምነቱ ጽድቅ ሆኖ እንደሚቈጠርለት የተነገረውን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪም ጽድቅ በእምነት የመቈጠሩ ጉዳይ ለአብርሃም ብቻ ሳይሆን ለእኛም እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር «ነገር ግን ተቈጠረለት የሚለው ቃል ስለ እርሱ ብቻ የተጻፈ አይደለም ስለእኛም ነው እንጂ፤ ስለ በደላችን አልፎ የተሰጠውን እኛን ስለማጽደቅም የተነሣውን ጌታችንን ኢየሱስን ከሙታን ባስነሳው ለምናምን ይቈጠርልን ዘንድ አለው» ይላል/ሮሜ4፡23‐25/፡፡
በእምነት የጸደቀ ሰው ግን በሥራም ይጸድቃል፤ ይህ ማለት ግን ሥራ በእግዚአብሔር ዘንድ ያጸድቃል ከማለት በፍጹም የተለየ ነው፤ በሥራ መጽደቅ በእምነት የተገኘው ጽድቅ በሰው ዘንድ በሚታይ ሥራ መረጋጡን የሚያመለክት ነው፡፡ እንዲሁም እውነተኛ እምነትን ተከትሎ ለሚሠራው መልካም ሥራ በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት የጽድቅ አክሊልን በብድራት መቀበልን የሚያሳይ ነው፡፡ ይህም በእምነት የጸደቁ ሰዎች የሥራቸውን ዋጋ ይቀበላሉ ማለት ነው እንጂ ሰዎች የሚጸድቁት ገና ያን ጊዜ ነው ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ሰውን የሚያጸድቀው እምነት ቀድሞውኑ ከሥራው ጋር አብሮ ያደርግ እንደነበር እንመለከታለን፤ ይህም ማለት በኋላ ይገለጥ ዘንድ ያለው ሥራ በእምነት ውስጥ ተሰውሮ እንደነበር እናያለን ማለት ነው፤ «ሰው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራም እንዲጸድቅ ታያላችሁ» ማለትም በሥራ ሊገለጥ በሚችል እውነተኛ እምነት የጸደቀ ሰው በኋላ በሥራውም ይጸድቃል ወይም መጽደቁ በድጋሚ ይረጋገጣል፣ ብድራትን ይቀበላል፣ ይሸለማል ማለት ነው እንጂ በእግዚአብሔር ዘንድ ለመጽደቅ ሰው በክርስቶስ ማመኑ ብቻውን በቂ ስለማይሆን ሥራም መሥራት ያስፈልገዋል ማለት አይደለም፡፡
የእውነተኛ እምነት ትክክለኛ ገጽታ በጊዜውም ይሁን ቈይቶ በሥራ ሊገለጥ የሚችል መሆኑ ነው፡፡ የእስራኤል አባት በሆነው በአብርሃም እምነት የተመለከትነውም ይህንን ነው፡፡ ከአሕዛብ በሆነችው በረዓብ እምነትም የምንማረው ይህንኑ እውነታ ነው፤ ስለዚህ በመቀጠል የረዓብ ማስረጃነት ቀርቧል፤ «እንደዚሁም ጋለሞታይቱ ረዓብ ደግሞ መልእክተኛቹን ተቀብላ በሌላ መንገድ በሰደደቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቀችምን?» ይላል/ቊ.25/፡፡ ከኢያሱ 2፡9‐11 ባለው ክፍል ረዓብ ለመልእክተኞቹ የተናገረችውን ስናነብ እርስዋ በእስራኤል አምላክ ያመነችው እግዚአብሔር የኤርትራን ባሕር በእስራኤል ልጆች ፊት እንዳደረቀና ጠላቶቻቸውን ሁሉ እንዳጠፋላቸው እርስዋና ወገኖችዋ በሰሙ ጊዜ መሆኑን እንረዳለን፤ ይህንንም ስትገልጥ «እግዚአብሔር ምድሪቱን እንደሰጣችሁ እናንተንም መፍራት በላይችን እንደወደቀ፣ በምድሪቱ የሚኖሩት ሁሉ ከፊታችሁ እንደቀለጡ አወቅሁ፤ ከግብፅ ምድር በወጣችሁ ጊዜ እግዚአብሔር የኤርትራን ባሕር ባደረቀ ጊዜ በዮርዳኖስ ማዶ በነበሩት እናንተም ፈጽማችሁ ባጠፋችኋቸው በሁለቱ በአሞራውያን ነገሥታት በሴዎንና በዐግ ያደረጋችሁትን ሰምተናል፤ ይህንንም ሰምተን ልባችን ቀለጠ» ብላለች/ቊ.9/፡፡ እንዲሁም በመቀጠል «አምላካችሁ በላይ በሰማይ በታችም በምድር እርሱ አምላክ ነውና ከእናንተ የተነሣ ከዚያ ወዲያ ማንም ነፍስ አልቀረለትም» ብላለች፤ በዚህ ቃል ረዓብ በእግዚአብሔር ያመነችው መልእክተኞቹን ተቀብላ በሌላ መንገድ ከመስደድዋ በፊት መሆኑን እናውቃለን፤ ስለሆነም በእግዚአብሔር ዘንድ እርስዋ እንደ አብርሃም ሁሉ ባመነች ጊዜ የጸደቀች ወይም ተቀባይነት ያገኘች እንደሆነች እንገነዘባለን፤ እንዲሁም ደግሞ መልእክተኞቹን ተቀብላ በሌላ መንገድ በሰደደቻቸው ጊዜ በሥራም ጸድቃለች ወይም ተረጋግጦላታል፤ በእርስዋም ሕይወት እምነት ከሥራ ጋር ያደርግ እንደነበር እናስተውላለን፤ ይህ አባባል ሥራ ከእምነት ጋር ያደርግ ነበር ከሚለው አባባል የተለየ ነው፤ በዋናነት እየተነገረለት ያለው እምነት ነው፤ እምነት ከሥራ ጋር ያደርግ ነበር ሲባል ያ እምነት በውስጡ ሰውሮ የያዘው ያልተገለጠ ሥራ እንዳለው የሚያሳይ ነው፤ ይህ እምነት ግን በውስጡ ይህን ሥራ ካልያዘ ማለትም ሥራ የተዋሐደው ካልሆነ የሞተ እምነት ነው፤ በቊ 26 ላይ ይህን በተመለከተ ሲናገር «ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደሆነ እንዲሁ ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው» ይላል፤ በእግዚአብሔር ዘንድ/ፊት/ መዳን በእምነት ነው ሲባልም በእንዲህ ያለ የሞተ እምነት ነው ማለት አይደለም፤ በውስጡ ሥራ በተዋሐደው እውነተኛ እምነት ነው ማለት ነው እንጂ፤ ይህ በእምነት ውስጥ በሐሳብ ደረጃ ተሰውሮ የነበረ ሥራ የሚገለጥበትን መስክ ሲያገኝ ከዚያ እምነት ውስጥ ወጥቶ በሰው ዘንድ በሚታይ መልኩ ይገለጣል፤ ነገር ግን ያን ጊዜ ያ ሰው እንደ አዲስ በእግዚአብሔር ፊት ገና መጽደቁ አይደለም፤ ቀደም ብሎ የጸደቀው ሰው አሁንም የጸደቀ መሆኑ በሥራው በሰው ፊት ይረጋገጥለታል ማለት ነው እንጂ፤ በሰማይም የሥራው ዋጋ የሆነውን የጽድቅ ብድራቱንም በቅዱሳን ሁሉ ፊት ያገኛል፡፡