በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት መኖር እንዴት እንደሚገባ ታውቅ ዘንድ እጽፍልሃለሁ፤ ቤቱም የእውነት ዓምድና መሠረት፥ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ነው።(1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 3:15)
1BIBLE
በመጀመሪያ እግዚአብሔር.........................................

የመንግሥተ ሰማያት መክፈቻዎች

/ማቴ.16፡18-19/

«እኔም እልሃለሁ፤ አንተም ጴጥሮስ /petros-ፔትሮስ/ ነህ፤ በዚችም አለት /petra-ፔትራ/ ላይ ቤተክርስቲያኔን እሠራለሁ፤ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም፤ የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል» /ማቴ.16፡18-19/፡፡

«እኔም እልሃለሁ፤ አንተም ጴጥሮስ /petros-ፔትሮስ/ ነህ፤ በዚችም አለት /petra-ፔትራ/ ላይ ቤተክርስቲያኔን እሠራለሁ፤ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም፤ የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል» /ማቴ.16፡18-19/፡፡

ቤተክርስቲያኑን «ኢየሱስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነው» በሚለው እውነት ላይ የሚገነባው ራሱ ጌታ ኢየሱስ ሲሆን ይህችም ቤተክርስቲያን «ሁለት ወይም ሦስት» ወይም ከዚያ በላይ ሆነው፣ ከዓለም ተለይተው በሌላ ስም ሳይሆን በራሱ በጌታ በኢየሱስ ስም በሚሰባሰቡና እርሱ ቀደም ሲል በምድር ላይ ይዞት የነበረውን ስፍራ ይዘው በሚገኙ የእውነተኛ አማኞች አንድነት የምትታይ ናት፡፡ ስለሆነም ወደዚህች ባሕርይዋ ሰማያዊ ወደሆነችው፣ ጌታ ኢየሱስም ራስ ወደሆነላት ወደአንዲቱ የክርስቶስ አካል ሰዎች የሚጨመሩት እንዴት ነው የሚለውን ማጤኑ ከላይ ለጴጥሮስ የተነገረውን የመንግሥተ ሰማያት መክፈቻዎች ጉዳይ ለመረዳት በር ይከፍታል፡፡ በዚህ ረገድም ሰዎች ወደዚያች ኅብረት ብልት ሆነው የሚገቡት በመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ሲያብራራ «አይሁድ ብንሆን የግሪክ ሰዎችም ብንሆን ባሪያዎችም ብንሆን ጨዋዎችም ብንሆን እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናል» ይለናል /1ቆሮ.12፡12-13/፡፡ ይሁን እንጂ መንፈስ ቅዱስ ሰዎችን ወደዚህች የክርስቶስ አካል የሚጠራው አስቀድሞ ብልት በሆኑ አማኞች በኩል መሆኑም የማይካድ እውነት ነው፡፡ የእነዚህም ሰዎች አገልግሎት ወይም ምስክርነት እጅግ ጠቃሚ ከመሆኑም ባሻገር በተሰባኪዎች ዘላለማዊ ዕጣ ፈንታ ላይ ወሳኝነት አለው፤ ስለዚህም ነገር ሐዋርያው ሲያስረዳ «የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል» ካለ በኋላ «እንግዲህ ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ባልሰሙትስ እንዴት ያምናሉ? ያለሰባኪስ እንዴት ያምናሉ?» በማለት የሰባክያን አገልግሎት እንደምን ወሳኝ እንደሆነ ይናገራል /ሮሜ10፡13-14/፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መሰበኩ ብቻ ተሰባኪውን የዚያች የእውነተኛይቱ ጉባኤ ብልት እንዲሆን የማያደርገው መሆኑም ሌላው እውነታ ነው፤ የተሰበከለት ሰው ስብከቱን አምኖ መቀበሉና አለመቀበሉ ከስብከት ቀጥሎ ጠቃሚ የሆነ ወሳኝ ነገር ነው፡፡ ተሰባኪው ስብከቱን አምኖ ቢቀበል መንፈስ ቅዱስ ወደዚያች ጉባኤ ብልት አድርጎ ይጨምረዋል፤ የተሰበከለትን ባያምነው ደግሞ አለማመኑ ኃጢአት ይሆንበታል፤ ብልት ሆኖ ወደ ክርስቶስ አካል አይጨመርም፤ «ባለማመናቸው ጠንቅ ሊገቡ እንዳልተቻላቸው እናያለን» ተብሎ ስለቀደሙት ሕዝበ እስራኤል እንደተነገረ /ዕብ.3፡19/ ያው ወደ ክርስቶስ አካል ብልት ሆኖ እንዲገባ የተጠራበት የምስክርነት ቃል ሰውን እንዳይገባ ያደርገዋል፤ እንደዚሁም ጌታ «እኔም መጥቼ ባልነገርኋችሁስ ኃጢአት ባልሆነባቸውም ነበር፤ አሁን ግን ለኃጢአታቸው ምክንያት የላቸውም» /ዮሐ.15፡22/ ሲል እንደተናገረው ነው፡፡ በተጨማሪም ቃሉ «በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል» ይላልና የሰማነውን ቃል ማመን አሁኑኑ ከፍርድ የዳንን/የተፈታን/ ሰዎች ሲያደርገን አለማመን ደግሞ አሁኑኑ የተፈረደብን/የታሰሩ/ ሰዎች ያደርገናል /ዮሐ.3፡18/፡፡

በተጨማሪም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ወራቱ በጊዜው ለነበሩ ጻፎችና ፈሪሳውያን የተናገረው ሐሳብ ሌላው የተነሣንበትን ምንባብ ለማብራራት የሚያስችለን ሆኖ ይገኛል፤ ጌታችን ለእነዚያ በዘመኑ መጻሕፍትን እናውቃለን መንፈሳዊነትንም ይዘናል ለሚሉ ነገር ግን የመጻሕፍትን ሐሳብ ለሚያጣምሙ ሕዝቡን ደግሞ «ሕግን የማያውቅ ርጉም ነው» /ዮሐ.7፡49/ እያሉ ከእግዚአብሔር እውቀት እንዲገለል አድርገው ለነበሩት ሰዎች «እናንተ ሕግ አዋቂዎች የእውቀትን መክፈቻ ስለወሰዳችሁ ወዮላችሁ፤ ራሳችሁ አልገባችሁም፤ የሚገቡትንም ከለከላችሁ» ሲል ተናገራቸው /ሉቃ.11፡52/፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በማቴዎስ ወንጌልም «እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን መንግሥተ ሰማያትን በሰው ፊት ስለምትዘጉ ወዮላችሁ፤ እናንተም አትገቡም፤ የሚገቡትንም ትከለክላላችሁ» ሲል ተናግሯል /ማቴ.23፡13/፡፡

እነዚህ ሰዎች መንግሥተ ሰማያትን የዘጉት እንደምን ነው? ቢባል መልሱ ህጉን ባለማስተማርና በማጣመም ነው የሚል ይሆናል፡፡ ስለሆነም ከላይ የጠቀስናቸው ሁለት ሐሳቦች የመንግሥተ ሰማያት መክፈቻ ወይም ቁልፍ እግዚአብሔር ኃጥኣንን ወደራሱ የሚጠራበት በሰዎች ያልተጣመመ ትክክለኛ የቃሉ ምስክርነት እንደሆነ ያሳዩናል፡፡ ይህንን ምስክርነት ሰጥቶ ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር የመጥራትን ጥሪ መቀበልም መክፈቻውን መቀበል ነው፤ መስበክና ማስተማርም መክፈቻውን ሥራ ላይ ማዋል ነው፤ ምስክርነቱን ሰዎች ሳይቀበሉ ሲቀሩ የተፈረደባቸው ወይም የተዘጋባቸውና የታሰሩ ይሆናሉ፤ ምስክርነቱን ሲቀበሉ ደግሞ ወደ መንግሥተ ሰማያት ለመግባት ከፍርድ የዳኑና የተፈቱ ይሆናሉ፤ በዚህ መንገድ ሰባኪው ቁልፉን ይጠቀማል፤ ማለትም ያስራል፤ ይፈታል፡፡ ለጴጥሮስም የተባለው ይኸው ነው፡፡

መታሰርና መፈታት

የተሰባኪዎች መታሰርና መፈታት የሰባክያን ቀጥተኛ ውጤት ሳይሆን መክፈቻ የሆነው የእግዚአብሔር ቃል በሰሚዎች ላይ የሚያመጣው ውጤት ነው፡፡ ሰዎቹን ማሰርና መፍታት የጴጥሮስ ቀጥተኛ ድርሻ አይደለም፤ ከጴጥሮስ የሚጠበቀው የተሰጠውን የወንጌል ሰባኪነት ጸጋ ሥራ ላይ ማዋል ነው፤ ልብ እንበል፤ ይህ ሰዎችን «ተፈቱ» ወይም «ታሰሩ» ብሎ በአፍ ከመናገር ወይም ፍርድን ከመግለጥ ወይም ከማወጅ በእጅጉ የተለየ ነው፡፡ የሰዎች መፈታትም ሆነ መታሰር የመክፈቻው ውጤት እንጂ የጴጥሮስ ፍርድ ወይም ፍላጎት አይደለም፤ የመንግሥተ ሰማያት መክፈቻ የሆነው የእግዚአብሔር ቃል በሰው ልብ ላይ እንዲሠራ ሲደረግ ውጤት አለው፤ ውጤቱም አንዳንዶችን ለእምነት ማብቃቱ ሲሆን አንዳንዶችን ደግሞ በእልከኝነታቸው ምክንያት በክህደት እንዲገለጡ ማድረጉ ነው፤ አንዱ እሳት ሰሙን ሲያቀልጥ ሸክላውን ደግሞ ከፊት ይልቅ ጠንካራ ያደርገዋል፤ የእግዚአብሔር ቃልም በሰዎች ላይ ተመሳሳይ ውጤት ያስከትላል፡፡

ስለሆነም ጴጥሮስ በተሰጠው መክፈቻ ማለትም በወንጌል ቃል ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንዲገቡ ለማድረግ ሲሰብክና ሰዎች አምነው በመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ወደ ክርስቶስ አካል ሲገቡ መክፈቻውን ተጠቅሞ በምድር እየፈታ ነበር፤ ሰዎች ምስክርነቱን አንቀበልም ሲሉ ደግሞ «ባለማመናቸው ጠንቅ» ወይም «ቃሉ ከሰሚዎቹ ጋር በእምነት ስላልተዋሐደ» /ዕብ.4፡2/ ወደ መንግሥተ ሰማያት እንዳይገቡ ሆነዋልና በምድር የታሰሩ መሆናቸውን እየገለጠ ነበር፡፡ ለምሳሌ ያህልም በበዓለ ሃምሳ ዕለት ጴጥሮስ ሲሰብክ ሦስት ሺህ ያህል ነፍሳት ወደ ቤተክርስቲያን አምነው ሲጨመሩ /ሲፈቱ/ እንመለከታለን፤ እንደዚሁም በሌላ ወቅት ጴጥሮስ የሰበከውን ቃል አምነው ብዙዎች ወደ ሐዋርያት ሲጨመሩ /ሲፈቱ/ በስብከቱ ደስ ያልተሰኙ ሌሎች ደግሞ በሐዋርያት ላይ «እጃቸውን ጭነውባቸው» ወደ ክርስቶስ ጉባኤ ሳይገቡ እንደቀሩ /እንደታሰሩ/ እናነባለን /የሐዋ.ሥ.4፡3-4/፡፡

ስለሆነም የቁልፉን ያዥ ድርሻና የቁልፉን ውጤት መለየት ይኖርብናል፡፡ ቁልፉን በሥራ ላይ ማዋል ማለትም ቃሉን መስበክ ነው፤ ቃሉን መስበክ የጴጥሮስ ድርሻ ነው፤ የሰዎች መታሰርና መፈታት መክፈቻው በሰዎቹ ምላሽ ላይ ተመርኩዞ የሚያመጣው ውጤት ነው፡፡

ሰማይና ምድር

በመቀጠል ደግሞ «በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድር የምትፈታው ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል» በሚለው አባባል ውስጥ ያለውን የሰማይና የምድር ግንኙነት እንመለከታለን፡፡ ይህም ማለት ጴጥሮስ ወንጌሉን እንደመለኮት ፍርድ ከሰበከ ያለጥርጥር ተሰባኪው ለወንጌሉ የሚሰጠው ምላሽ በሰማይ እውቅናና ክትትል አለው ማለት ነው፡፡ ይህም ምድር ላይ እንደ ሰማይ ፍርድ ለተሠራው ሥራ ሁሉ ሰማያዊ ክትትል፣ እውቅናና ድጋፍ እንዳለ የሚያመለክት ነው፡፡ ስለዚህ አገልጋዩ የሚያገለግለው ብቻውን ሳይሆን መለኮታዊ መገኘትና ክትትል ባለበት ሁኔታ ውስጥ ነው ማለት ነው፡፡ ሰዎች የሰባኪውን ቃል አምነው ሲቀበሉ መቀበላቸው በእግዚአብሔር ዘንድ ወዲያውኑ የታወቀ ሲሆን አለመቀበላቸውም ወዲያውኑ በእግዚአብሔር ፊት ለፍርድ የተዘጋጁና የተፈረደባቸው ከእግዚአብሔር መንግሥትም የተገለሉ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡ ስለዚህ ሰዎች በምድር ላይ ለሚሰሙት የወንጌል ቃል የሚሰጡት ምላሽ በእጅጉ ዘላለማዊ ማንነታቸውን የሚወስን ነው ማለት ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ሰዎች በምድር ላይ በወንጌል ስብከት አምነው ወደ ክርስቶስ አካል ካልተጨመሩ በቀር ዛሬም ሆነ ወደፊት በሰማይ ላይም ያልተጨመሩ ሆነው እንደሚቀሩ የሚያሳይና እንደዚሁም እንደፍርዱ አሠራር የሚሰጠውን ምስክርነት አምነው ወደ ክርስቶስ አካል የተጨመሩት ደግሞ መጨመራቸው በሰማይም ጭምር የተረጋገጠና ይህ መብታቸውና ያገኙትም ስፍራ ሰማያዊ እውቅናና ድጋፍ ያለው መሆኑን ከዚህ ምንባብ መረዳት እንችላለን፡፡ በምድር ሳሉ ቃሉን ያላመኑትና የካዱት ሁሉ በሰማይም የካዱ ሆነው ይታወቃሉ፤ ከሞቱ በኋላ ወደ ክርስቶስ አካል መጨመርም አይችሉም፤ ሰው ነፍሱ ከሥጋው በምትለይበት ወቅት የነበረው ማንነቱን ሰማይ ላይ ሊቀይር ወይም ሊያሻሽል አይችልም፤ በምድር ላይ የነበረውን ማንነቱን ይዞ ወደዘላለም ስፍራው ይሄዳል እንጂ፡፡ ከነኃጢአቱ ከሞተ በሰማይም ኃጢአተኛ ነው፡፡ በምድር ላይ በጌታ በኢየሱስ ቤዛነት ከኃጢአቱ ድኖ በሥጋ ቢሞት ደግሞ ከዚያን በኋላ ማንነቱን ሊያበላሽበት የሚችል ምንም ኃይል የለም፤ ምክንያቱም በምድር ላይ ከኃጢአቱ ሲድን መዳኑ በሰማይም እውቅና አግኝቷልና፡፡ ስለሆነም በዚህ ምድር ስለጌታ ኢየሱስ የሚሰጠውን የቃሉን ምስክርነት አምኖ ራስ ወደሚሆን ወደእርሱ የተጠጋ አማኝ በአካለ ሥጋ እያለም በእጅ ወዳልተሠራችውና ራሱ ጌታ ኢየሱስ ወዳለባት ሰማያዊ መቅደስ በመንፈስ የመግባት በዚያም ሆኖ የመጸለይ መብት አለው /ዕብ.10፡19-20/፤ ከዚህም ባሻገር እንዲህ ያለው አማኝ ነፍሱ ወደ ጌታ ሳትሄድ ከወዲሁ «ወደ ጽዮን ተራራና ወደሕያው እግዚአብሔር ከተማ፣ ወደ ሰማያዊቱም ኢየሩሳሌም፣ በደስታም ወደ ተሰበሰቡት ወደ አእላፋት መላእክት፣ በሰማያትም ወደ ተጻፉ ወደ በኵራት ማኅበር፣ የሁሉም ዳኛ ወደሚሆን ወደ እግዚአብሔር፣ ፍጹማን ወደሆኑት ወደ ጻድቃን መንፈሶች፣ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ወደሚሆን ወደ ኢየሱስ፣ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገር ወደመርጨት ደም» ደርሷል /ዕብ.12፡22-24/፡፡

ስለሆነም ምስክርነቱን በተመለከተ ሰዎች ዛሬ በምድር ላይ የሚወስኑት ውሳኔ ምድራዊ ውሳኔ ብቻ ሳይሆን በሰማይ ላይም በጌታ ፊት የሚታወቅ ውሳኔ መሆኑን አውቀው ሊጠነቀቁ ይገባቸዋል፡፡ በምድር ላይ ካልተሻሻለም ውሳኔው በሰማይ ላይ ሊሻሻል አይችልም፡፡ ወንጌሉን እምቢ አንቀበልም ሲሉም እምቢ ያሉት የሚመሰክረውን ምስክር ብቻ አይደለም፤ ምስክርነቱንና ምስክሩን የላከውን ጌታ ጭምር እንጂ፡፡ በመሆኑም ሰዎች በጊዜው አሁን በምድር ላይ እየተሰጠ ያለውን ምስክርነት ሊቀበሉና ወደ ክርስቶስ ሊከማቹ ይገባል፡፡ እዚህ ላይ አንባቢው ልብ ይበል፡፡

ከዚህ በመቀጠል ደግሞ እንዲህ ያለውን ግልጥና የተባረከውን የጌታ ኢየሱስን ንግግር በማስታከክ የተፈጠሩና ለብዙ ዘመናት የተንሠራፉ በእጅጉ ስህተት የሆኑ አመለካከቶችን በመዘርዘር እንመለከታቸዋለን፡፡ አላማውም ሰዎችን ለመተቸት ሳይሆን የተመሠረቱት የስህተት አተሳሰቦች ከዚህ ምንባብ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው መሆናቸውን ለማሳየት ነው፡፡ ስለሆነም በጥቅሉ ቃሉ የሚከተሉትን አመለካከቶች የሚያሳይ አይደለም፡፡www.ewnet.org.et/btm_files/aclesia.htm


 
ከእርሱም የሰማናት ለእናንተም የምናወራላችሁ መልእክት። እግዚአብሔር ብርሃን ነው ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም የምትል ይህች ናት።(1ኛ የዮሐንስ መልእክት 1:5)
This website was created for free with Own-Free-Website.com. Would you also like to have your own website?
Sign up for free