በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት መኖር እንዴት እንደሚገባ ታውቅ ዘንድ እጽፍልሃለሁ፤ ቤቱም የእውነት ዓምድና መሠረት፥ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ነው።(1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 3:15)
1BIBLE
በመጀመሪያ እግዚአብሔር.........................................

የእግዚአብሔር በግ

«እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ »ዮሐ1፡29፡፡

 

 

እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ካለው ፍቅር የተነሣ በኃጢአት ምክንያት ከእርሱ የተለየውንና የራቀውን ሰው ሊያድነውና ከእርሱ ጋር ኅብረት ሊያደርግ ሲፈልግ በሰው ፈንታ ቤዛ ሆኖ የሚሞት መሥዋዕትን አዘጋጀለት፤ በብሉይ ኪዳን ዘመን ሰዎች ስለኃጢአታቸው የበግ መሥዋዕትን በማቅረብ ወደ እግዚአብሔር ይቀርቡ ነበር፤ ይሁንና ያ የበግ መሥዋዕት /ዘሌ.4፡27-35/፡፡ ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርባቸው መሥዋዕቱን ባቀረቡበት በዚያ ጊዜ ብቻ ሲሆን ስርየት የሚያገኘውም የአቅራቢው ኃጢአት ብቻ ነበር፤ በዓመት አንድ ጊዜ በሚከበረው በስርየት በዓል ስለእስራኤል ሕዝብ የሚቀርበው የኃጢአት መሥዋዕትም ቢሆን ስርየት የሚያስገኘው የእስራኤልን ማኅበር ኃጢአት ብቻ ነበር እንጂ የዓለምን ኃጢአት አልነበረም/ዘሌ.16/፤ እንደዚህም ሆኖ ለጊዜው ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ የሚያስችል ከመሆን አልፎ የብሉይ ኪዳን የእንስሳት መሥዋዕት ኃጢአትን ማስወገድ አልቻሉም ነበር፡፡ ይህን በተመለከተ የእግዚአብሔር ቃል ሲናገር ‹የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን እንዲያስወግድ የማይቻል ነውና› ይላል/ዕብ.10፡4/፡፡

በዚህ በጸጋው ዘመን ግን እግዚአብሔር የአንድን አማኝ ወይም የእስራኤልን ኃጢአት ብቻ ሳይሆን የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ መሥዋዕት ለሰው ልጅ ሰጥቷል፤ ይህንንም «እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ» ብሎ መጥምቁ ዮሐንስ በዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ ኃጢአታቸውን ለተናዘዙ ሰዎች አስተዋውቋል፡፡ በዚያ ወቅት በቤተመቅደሱና በመሠዊያው ዙሪያ የነበሩት ፈሪሳውያንና ተከታዮቻቸው ሰውን ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርብ አገልግሎት መስጠት አልቻሉም ነበር፤ ጊዜው በአይሁድ ዘንድ የውድቀት ጊዜ ነበር፤ ከእግዚአብሔር ቃልና ትእዛዝ ይልቅ የሽማግሌዎች ወግ የሚጠበቅበት፣ ግብዝነትና አስመሳይነት የበዛበት፣ በሌላው ኃጢአት ላይ የሚፈርዱ ሰዎች ራሳቸው ያንኑ ኃጢአት የሚያደርጉበት ዘመን ነበር፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር በሥጋ የተገለጠውን ልጁን ለእስራኤል ለመግለጥ የመጥምቁ ዮሐንስን የምስክርነት አገልግሎት አዘጋጀ፡፡ ብዙ ሰዎችም ኃጢአታቸውን በመናዘዝ በንስሐ ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ፤ ይሁንና በዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ በሕጉ መጽሐፍ እንደታዘዘው ስለኃጢአታቸው በእነርሱ ፈንታ ኃጢአታቸውን ተሸክሞ የሚሞትላቸውን የበግ መሥዋዕት አላቀረቡም ነበር፤ ስለኃጢአታችን የቀረበ የበግ መሥዋዕት የት አለ? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ሊሆን እንደሚችል ማሰብ ይቻላል፤ መጥምቁ ዮሐንስ ግን ‹ኢየሱስን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ› «እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ» ብሎ ልብን የሚያሳርፍ ምስክርነት ሰጣቸው፡፡ በዚህም «የኃጢአታቸው ስርየት የሆነውን የመዳንን እውቀት ለሕዝቡ ትሰጣለህ» ብሎ አባቱ ዘካርያስ ስለእርሱ የተናገረው ትንቢት ተፈጸመ /ሉቃ.1፡77/፡፡

ዛሬም በየሥርዓተ አምልኮው በሚከናወኑ የተለያዩ ሥርዓቶች እንዲሁም እጅግ በዝቶ በሚታየው መንፈሳዊ ውድቀት የተነሳ በኃጢአታቸው እየተጨነቁ ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ ያልቻሉ ብዙ ሰዎች በውድቀት ዘመን እግዚአብሔር ያዘጋጀው ይህ የመጥምቁ ዮሐንስ አገልግሎት ያስፈልጋቸዋል፤ ይኸውም እግዚአብሔር ኃጢአታችንን ለማስወገድ ለዓለም ሁሉ ከሰጠው ከራሱ በግ ጋር ማገናኘት ነው፤ ይህም የእግዚአብሔር በግ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ስለእርሱ አስቀድሞ «ተጨነቀ ተሠቃየም አፉንም አልከፈተም ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት በሸላቾቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ እንዲሁ አፉን አልከፈተም» የሚል ቃል በትንቢት ተነግሯል /ኢሳ.53፡7/፡፡ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ሲመለስ ያነብ የነበረውም ስለእግዚአብሔር በግ የሚናገረው ይህ የመጽሐፍ ክፍል ነበረ፡፡ ወንጌላዊው ፊልጶስም ከዚህ መጽሐፍ ጀምሮ ስለኢየሱስ ወንጌልን ሰበከለት፤ እርሱም በኢየሱስ አምኖ በመጠመቅ በታላቅ ደስታ ወደ አገሩ ተመለሰ /የሐ.ሥ.8፡26-39/

በሮሜ 6፡23 ላይ «የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነው» ተብሎ ተጽፏል፤ በዚህ እውነታ ምክንያት ኃጢአተኝነታቸውን የሚያውቁ ሁሉ በሞት ፍርሃት ተውጠው ሲጨነቁ ይኖራሉ፤ ነገር ግን ኢየሱስ የእግዚአብሔር በግ ሆኖ በመምጣት በቀራንዮ መስቀል ላይ ኃጢአታችንን ሁሉ በእንጨት ላይ ተሸክሞ ስለሰው ሞቷል፤ ስለሆነም በኃጢአትና በሞት ፍርሃት ውስጥ ያሉ ሁሉ ኢየሱስ የሞተው ስለእኔ ነው ብለው ቢያምኑ እነርሱ እንደማይሞቱ ስለሚያውቁ ከዘላለም ሞት ይድናሉ፤ በምትኩ ግን የዘላለም ሕይወትን ይቀበላሉ፡፡ ቃሉ «የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነው» ካለ በኋላ «የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ነው» ይላል፡፡ ስለዚህ በቀደመው ኪዳን የነበረው ኃጢአተኛ እጁን በበጉ ላይ ጭኖ ራሱን ከመሥዋዕቱ ጋር እንደሚቆጥር ሁሉ/ዘሌ.4፡29፣33/ ዛሬም በወንጌል የተጠራ ማንኛውም ኃጢአተኛ በቀራንዮ ላይ የኃጢአት መሥዋዕት ሆኖ ከቀረበው የእግዚአብሔር በግ ጋር ሊቈጥር ወይም በእምነት ከክርስቶስ ጋር ሊሰቀል ይገባዋል፡፡ ያን ጊዜም የእግዚአብሔር ጽድቅ ለእርሱ ይቈጠርለታል፡፡ የዘላለም መዳንን ወይም የዘላለም ሕይወትን ያገኛል፡፡www.ewnet.org.et/btm_files/Medan2.htm


 
ከእርሱም የሰማናት ለእናንተም የምናወራላችሁ መልእክት። እግዚአብሔር ብርሃን ነው ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም የምትል ይህች ናት።(1ኛ የዮሐንስ መልእክት 1:5)
This website was created for free with Own-Free-Website.com. Would you also like to have your own website?
Sign up for free