በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት መኖር እንዴት እንደሚገባ ታውቅ ዘንድ እጽፍልሃለሁ፤ ቤቱም የእውነት ዓምድና መሠረት፥ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ነው።(1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 3:15)
1BIBLE
በመጀመሪያ እግዚአብሔር.........................................

The Secret of Orthodox

ድርብ ታቦት ከየት መጣ? ተሸክሞ መዞርስ ለምን አስፈለገ?
ድርብ ታቦት ተብሎ መታወቅ የጀመረው በግራኝ መሐመድ ዘመን ነው ይባላል። ግራኝ መሐመድ አብያተ ክርስቲያናትን ሲያቃጥል ቀሳውስት ታቦቱን እያሸሹ ወደአልተቃጠለ ቤተ ክርስቲያን እየወሰዱ ይደርቡ ነበር፣ አንዳድ ታቦቶች ሌላ ቤት ተሥርቶላቸው የተመለሱ ሲሆን አንዳዶች ግን በዚያው ተደረበው ቀርተዋል። ዛሬ በአንዳድ አብያተ ክርስቲያናት ከ40 በላይ ታቦቶች (የምሥክር ወረቀቶች)የመገኘታቸው ምክንያት ይኸው ነው። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን አንዳድ የጥቅም ደብተራዎች ድርብ ታቦትን የቢዝነስ ሥራ አደረጉት።

ድርብ ታቦት አሁን አሁን የቢዝነስ ጉዳይ ብቻ ነው። የሥጋውና ደሙ መሠዊያ ነው ብለው የሚሰብኩትን አያወጣቸውም። ምክንያቱም ሥጋና ደሙ የሚሠራው በአንድ ታቦት ብቻ ነውና መደራረቡ ለምን አስፈለገ? እንላለን። እኛ ድርብ ታቦት የገንዘብ ማግኛ ዘዴ ነው ያልበንትን ምክንያት ከተጨባጭ ማስረጃ ጋር እናቅርብ።

ለምሳሌ፤ ጎላ ሚካኤል ድሮ ሚካኤል ከመደረቡ በፊት የመንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን ነበር። በኋላ ግን ሕዝቡ መንፈስ ቅዱስን ባለማወቁ ወደዚያ ሊመጣና ገንዘብ ሊሰጥ ባለመቻሉ ሕዝቡ የለመደው ሚካኤል ተደረበ፣ ከዚያም ሕዝቡ መምጣትና ገንዘቡን ማዝነብ ሲጀምር ሚካኤል ከመንፈስ ቅዱስ መብለጡን ለማሳየት "ጎላ” ሚካኤል ተባለ። ጎላ ሚካኤል የመንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን የነበረ መሆኑን እስካሁን ድረስ "ጽርሐ ጽዮን” እየተባለ መጠራቱን ልብ ይበሉ።

ቀጨኔ መድኃኔ ዓለም ከጥንት ጀምሮ በመድኃኔ ዓለም የተሰየመ ነበር። ሕዝቡን መድኃኔ ዓለምን ባለማወቁና ገንዘብ ሊገኝ ባለመቻሉ ገብርኤል ተደረበ በሩ አካባቢም ትንሽ ቤተ መቅደስ ተሠርቶለት ትልቅ የገቢ ምንጭ ሆኗል። ሕዝባችን ከመድኃኔ ዓለም ይልቅ ገብርኤልን የሚያመልክ መሆኑ የታወቀ ነው። በነገራችን ላይ እስከዚህ ዘመን ድረስ በሌላ ታቦት ላይ ሲደረቡ የኖሩት ሦስቱ ታቦቶች ናቸው እነርሱም ማርያም፣ ሚካኤል፣ ገብርኤል ሲሆኑ አሁን አሁን ግን አርሴማና የሸንኮራው የሐንስ በብዛት እየተደረቡ ነው። እስከ ዛሬ በገብርኤል፣ በሚካኤል፣ በማርያም ላይ የተድረበባቸው ታቦት የለም እነርሱ ግን በሌላ ታቦት ላይ እየሄዱ መደረብን ይዘውታል። ተክለ ሃይማኖትና አቡነ አረጋዊ አስካሁን ተከባብረው ይኖሩ ነበር ማለት አንዱ ባንዱ ላይ አይደረብም ነበር አሁን በአሜሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ ተደራርበው እየኖሩ ነው። በተክለ ሃይማኖት ሽዋዎችን በአቡነ አረጋዊ ትግሬዎችን ለመያዝ ተብሎ የተደረገ ነው።

ድሮ ድሮ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድን የሚያመልከው አልነበረም በሸንኮራ እስኪታወቅ ድረስ። ለምሳሌ ጎጃም በረንዳ አካባቢ ያለው ወልደ ነጎድጓድ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን እውቅና በማጣቱ ገንዝብ ሊገኝ አልቻለም ነበር በኋላ ግን ማርያም ተደርባ ትልቅ የገቢ ምንጭ ፈጥራለች፣ እዚያው አንድ ግቢ ውስጥ ሁለት ቤተ ክርስቲያን ተሠርቶ ጥሩ ገቢ ተገኝቷል። በጎጃም በረንዳ አልታወቅ ብሎ የነበረው ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ፤ ሕዝቡ እስካሁን ባልለመደው በቦሌ መድኃኔ ዓለም ላይ ተደርቦ የካህናቱን ደሞዝ በሚገባ እየሰበሰበ ነው። በነገራችን ላይ ሕዝቡ ዮሐንስ መሆኑን እንጂ መጥምቁ ይሁን ወንጌላዊው ለይቶ አያውቅም፣ ብቻ ዮሐንስ ይሁን፣ ይህን እውቅና ያገኘውም በሸንኮራ ያድናል ስለተባለ ነው። በአሁኑ ሰዓት አርሴማ ሁሉንም እየቀደመች በብዙ ቦታ እየተደረበች ነው። እርሷ የወጣቱ አምላክ ሆናለችና ካህናቱም ቢዝነስ እየሠሩባት ነው።

ዛሬ በአዲስ አበባ ከ50 በላይ የተደራረበ የገብርኤልና የማርያም ቤተ ክርስቲያን ሲኖር የኢየሱስ ግን ሁለት ብቻ ናቸው ገነተ ኢየሱስና ገዳመ ኢየሱስ። ገነተ ኢየሱስ ገንዝብ ባለማምጣቱ ማርያም ተደርባለች አንድ ግቢ ውስጥ፡ሁለት ቤተ ክርስቲያን ተሠርቷል። ስለዚህ የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን በአዲስ አበባ አንድ ብቻ ይሆናል እርሱም ገዳመ ኢየሱስ ነው። እርሱስ የሰው ልጅ ግን እራሱን የሚያስጠጋበት የለውም ያለው ለዚህ አይደል?

ማጠቃለያ
እውነተኛው ታቦት የፈቃድ ወረቀት ስለሆነ በክብር መያዛችን አይከፋም ስጋውና ደሙን ብንሰዋበትም አይጎዳንም። ተሸክመነው የምንዞርበት ምክንያት ግን አይታወቅም፣ ለፌስቲባል ወይም ለባህል ድምቀት ከሆነ ጥሩነው፤ ለስግደትና ለአምልኮ ከሆነ ግን ትልቅ ስሕተት ነው ለማን ነው የምንሰግደው? ለምሳሌ ታቦቱ የሚካኤል ከሆነ ለሚካኤል መስገዳችን ነው ያርሴማም ከሆነ እንዲሁ? የሚካኤልና የሥላሴ ታቦት አንድ ላይ ቢወጡ ለማን ነው የምንሰግደው? ለሁለቱም የሚል መልስ ሊኖር ይችላል ሁለቱን ባንድ ጊዜ ማምለካችን ነው ማለት ነው? ለሚካኤል የምንሰግደውና ለሥላሴ የምሰግደው በምን ይለያል? እኛ ይህን ጥያቄ ያነሳነው ለማን መስገድ እንዳለብን ስለማናውቅ አይደለም ሰማይና ምድርን ለፈጠረው በሁሉ ለሚገኘውና ለተፈራው አምላክ ብቻ በመንፈስ እንሰግዳለን ለሌላ ለማንም አንሰግድም ዮሐ 4፥21-26 "እኔ እግዚአብሔር ነኝ ስሜ ይህ ነው ክብሬን ለሌላ ምስጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች አልስጥም‚ኢሳ 42፥8 ይላልና እኛም ለማንም አንሰጥም።

ድርብ ታቦት ለገንዘብ ነው ሌላ ምንም ምስጢር የለውም፣ ይህ የዘረፋ ስልት መቆም አለበት፣ ያታለልንበት ዘመን ያበቃ ይመስለናል፣ ሰውን ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔርንም ንቀናል ስለዚህ እግዚአብሔር ለክብሩ ተነሥቷል ሕዝባችንን ያዋረደውን ሁሉ ከንቱ ነገር እራቁቱን ሊያስቀረው ለሐፍረትና ለመሳቂያ ሊያደርገው ተነሥቷል። የሚመጣው ትውልድ የሚታለል አይደለምና ከወዲሁ እንንቃ።

የገንዘብ ጉዳይ ከሃይማኖት ጋር በመያያዙ ባዕድ አምልኮዎች ተስፋፍተዋል፣ እንደ እግዚአብሔር ቃል ያለሆኑ ልማዶችም ሕዝቡን አንቀው በመያዛቸው በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በመንፈሳዊ ሕይወቱ ነጻ መውጣት አልቻለም፣ የሀገሪቱ ችግር የሃይማኖት ችግር ነው፣ እንደ እግዚአብሔር ቃል ያለሆነ፣ ኦርቶዶክሳዊም ያልሆነ፣ የሩቅ ምሥራቅ አገሮች ልማድ ሥራ አስፈትቶን አደንዝዞንና አስንፎን ይገኛል። ይህ ተጠራርጎ መወገድ አለበት፣ ዘመኑ የተሐድሶ ነውና እንታደስ።



 
ከእርሱም የሰማናት ለእናንተም የምናወራላችሁ መልእክት። እግዚአብሔር ብርሃን ነው ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም የምትል ይህች ናት።(1ኛ የዮሐንስ መልእክት 1:5)
This website was created for free with Own-Free-Website.com. Would you also like to have your own website?
Sign up for free