በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት መኖር እንዴት እንደሚገባ ታውቅ ዘንድ እጽፍልሃለሁ፤ ቤቱም የእውነት ዓምድና መሠረት፥ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ነው።(1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 3:15)
1BIBLE
በመጀመሪያ እግዚአብሔር.........................................

የተረገሙ ሰባኪያን ወንጌል

“ነገር ግን እኛም ብንሆን ወይም የሰማይ መልአክ፣ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የተለየ ወንጌል ቢሰብክላችሁ እርሱ ለዘላለም የተረገመ ይሁን፡፡ ቀደም ብለን እንዳልነው አሁንም ደግሜ እላለሁ፣ ማንም ከተቀበላችሁት ሌላ የተለየ ወንጌል ቢሰብክላችሁ ፣ እርሱ ለዘላለም የተረገመ ይሁን፡፡” (ገላ 1፡8-9)
በገላትያ ያሉ አብያተክርስቲያናት በጅማሬአቸው እንዴት እንደ ነበሩ ጳውሎስ በመልዕክቱ ሲያስታውሳቸው፡- “ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ በፊት ለፊታችሁ በግልጥ ተስሎ ነበር” ይላቸዋል (ገላ.3፡1)፡፡ ቀደም ብሎ “ በክርስቶስ ጸጋ የጠራችሁን እርሱን ትታችሁ፣ ወደ ተለየ ወንጌል እንዲህ ፈጥናችሁ መዞራችሁ ደንቆኛል:: እንደ እውነቱ ከሆነ ሌላ ወንጌል የለም፡፡ የሚያደነጋግሩአችሁና የክርስቶስን ወንጌል ለማጣመም ጥረት የሚያደርጉ አንዳንድ ሰዎች አሉ” ብሎአቸዋል (ገላ. 1፡6 )፡፡
ልዩ ወንጌል ምንድነው
የተለየ ወንጌል የሚባለው የተሰቀለውን ክርስቶስ የመዳናችን (salvation) ማዕከል እንደሆነ እንዳናስተውል የሚያደርገን የተጣመመ ወንጌል ነው፡፡ ለምሳሌ የገላትያ አብያተክርስቲያናት በኢየሱስ ማመንን እንደያዙ የብሉይ ኪዳኑን የመገረዝ ሕግ እንዲጨምሩበትና ድነታቸውን እንዲያሟሉ የመከረና የአይሁድ እምነትን ከክርስትና የቀየጠ ትምህርት ነው ልዩ ወንጌል ተብሎ የተጠራው፡፡ “እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን” ሲል ጳውሎስ ለቆሮንጦስ ክርስቲያኖች በ1ቆሮ.1፡23 ላይ እንደጻፈው የእውነተኛው ወንጌል ማዕከል የተሰቀለው ክርስቶስ ብቻና ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ በክርስትና ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ በተሰባሰበ ጥቅስ በተደራጀ መልክ የሚሰበክ ማንኛውም ወንጌል ልዩ ወንጌል ይባላል፡፡ ሰባኪያኑም የሰማይ መላዕክት እንኩዋ ቢሆኑ የተረገሙ ናቸው፡፡
ይህ የብሉይ ኪዳን ቀያጭነት በቆሮንጦስ ቤተክርስቲያንም ሰይጣን አሽሉኮ በሾማቸው አይሁድ ክርስቲያኖች በኩል ገብቶአል (2ቆሮ.3፡13፤11፡3-15)፡፡ እንደውም ቤተክርስቲያኒቱ በሚሰበክላት “ሌላ ኢየሱስ” እና “የተለየ ወንጌል”፣ “የተለየ መንፈስ” እየተቀበለች ነገሩን በቸልታ አልፋዋለች ( 2ቆሮ.11፡4)፡፡
የዘመናችን የተረገሙ ሰባኪያን ወንጌል የቱ ነው
ይህ ከላይ ያነሳነው ብሉይ ኪዳናዊ ቀያጭነት በድንቅና ተአምራት ታጅቦ በሰይጣን አቀናባሪነት (2ቆሮ.11፡13-15) በብዙ ውዳሴ በፕሮቴስታንት መድረክ ላይ ገኖአል፡፡ ቤተክርስቲያን ከሙሴ ሕግ በታች አይደለችም ብሎ ያለን አዲስ ኪዳን ነው፡፡ ይህ ደግሞ በጌታ ከተደገሙት የፍቅር(ማቴ.22፡35-40) ፣ የአስርቱ ትዕዛዛት (ማቴ.5፡17-44) እና የአስራት ሕግ (ሉቃ.11፡42) በቀር የዘዳግም 28 የበረከትና መርገም ሕግም ለእስራኤል የተሰጠ እንጂ ለቤተክርስቲያን አይደለም፡፡ መገረዝ ለጤና ከሆነ እንጂ ለጽድቅ ቀርቶአል እያልን ዘዳግም 28 ግን አልቀረም ብንል ተሳስተናል፡፡ በእርሻችን ሁለት አይነት ዘር እንዳንዘራ፣ ከሁለት አይነት ነገር የተሠራ ልብስ እንዳንለብስ ተነገረውን ሕግ ለእሥራኤል እንጂ ለቤተክርስትያን እንዳልሆነ አንከራከራለን፡፡ የዘዳግም28 በረከቶችን ግን የብልጽግናችን መሠረት አድርገን እንሰበካለን፣እንሰብካለን፡፡ ትልቅ ስህተት! 
የዘመኑ የበረከት፣ የስኬት፣ የጤና እና የብልጽግና ሰባኪያን መሠረት ዘዳግም 28 ነው፡፡ የተሰቀለውን ክርስቶስ ከሙሴ ሕግ ቀይጠው ልዩ ወንጌል እንዲሰብኩ ሰያጣን የሾማቸው (2ቆሮ.11፡13-15) እግዚአብሔር ግን የረገማቸው ናቸው፡፡ “ እስራኤላውያን የፊቱ ማንጸባረቅ እየጠፋ ሲሄድ መጨረሻውን እንዳይመለከቱ ፊቱን በጨርቅ እንደ ሸፈነው እንደ ሙሴ አይደለንም፤ ነገር ግን ብሉይ ኪዳን በተነበበ ቁጥር ያ መሸፈኛ እስከ ዛሬ ድረስ ስላልተወገደ ልቡናቸው እንደደነዘዘ ነው፤ መሸፈኛው አሁንም አልተወገደም፤የሚወገደው በክርስቶስ ነውና፡፡ እስከ ዛሬም የሙሴ ሕግ በተነበበ ቁጥር መሸፈኛው ልቡናቸውን ይሸፍናል፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው ወደ ጌታ ዘወር ሲል መሸፈኛው ይወገዳል፡፡” (2ቆሮ 3፡13-16)
የቤተክርስቲያን ልቡና ዛሬም በነዚህ የተረገሙ ሰባኪያን ያ የብሉይ ኪዳን መሸፈኛ ተጥሎበት ደንዝዞአል፤ ክርስቶስንም መስቀሉንም መመልከት ተስኖታል፡፡ ስኬት፣ ብልጽግና እና ጤና ጣኦት ሆኖበታል፡፡ ቤተክርስቲያን የምድራዊ ነገር ምኞች አስክሮአታል፡፡ “ትለምናላችሁ ግን አትቀበሉም፤ ለራሳችሁ ሥጋዊ ደስታ በማሰብ በክፉ ምኞት ትለምናላችሁና፡፡ አመንዝሮች ሆይ፣ ከዓለም ጋር ወዳጅ መሆን የእግዚአብሔር ጠላት መሆን እንደሆነ አታውቁምን ስለዚህ የዓለም ወዳጅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል” (ያዕ.4፡3-4)፡፡ በተጨማሪ 1ዮሐ.1፡15-17 ይህንኑ ይደግምልናል፡፡
እነዚህ ሰባኪያን “መጨረሻቸው ጥፋት ነው፤ ሆዳቸው አምላካቸው ነው፤ ክብራቸው በነውራቸው ነው፤ ልባቸው ያረፈው በምድራዊ ነገር ላይ ነው” ፊሊጵ.3፡19፡፡ ቁጥር18 “ብዙዎች የክርስቶስ መስቀል ጠላቶች ሆነው ይመላለሳሉ” እንደሚል እንዲሁ የመስቀሉ ጠላቶች ሲሆኑ ነገር ግን የምድራዊ ነገር ወዳጆች ናቸው፡፡ የሕዝቡ ልብ ከመስቀሉ ይልቅ በምድራዊ ነገር እንዲያዝ ለማድረግ በትጋት እንዲሰሩ ሰይጣን በድንቅና ተአምራት ያጅባቸዋል፤ ከሕዝብ የሚዘርፉት ሰአራትና ስጦታ አበልጽጎአቸዋል (2ቆሮ.11፡20)፡፡ ሕዝቡ እንደነሱ”ሊባረክ” እያጨበጨበ በረከተ-መርገማቸውን “አሜን!” እያለ ይከተላቸዋል፡፡ ግን የተረገሙ ናቸውና ከመንገዳቸው ተመልሶ ንሰሐ ይገባ ዘንድ ያስፈልጋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የምድራዊ (ዓለማዊ) ነገር ወዳጅ የእግዚአብሔር ጠላት ነው ይላል፤ ጌታንና መስቀሉን አይወድም፡፡ “ጌታን የማይወድ ቢኖር የተረገመ ይሁን” ይላል የእግዚአብሔር ቃል 1ቆሮ. 16፡22፡፡ የተባረክን መስሎን ከገባንበት እርግማን በንስሐ እንመለስ፡፡ “አንድ ሰው ሁለት ጌቶችን ማገልገል አይችልም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወዳል፤ ወይም አንዱን አክብሮ ሌላውን ይንቃል፡፡ እግዚአብሔርንና ገንዘብን በአንድነት ማገልገል አይቻልም፡፡” (ማቴ 6፡24) 
እስራኤል ለምርኮ የተዳረገችበት ኃጢአቶች፡- (1)ጣኦት አምልኮ፣ (2) የማህበራዊ ፍትህ መጉደልና (3) እነዚህ ኃጢአቶቹዋን ለመሸፈን የምታደርገው የአምልኮ (የመስዋዕት) ማደናገሪያ ነበሩ፡፡ በተለይ ሦስተኛውን ማለትም ይህንን አምልኮ እንደሚጸየፍ ጌታ ደጋግሞ ይነግራቸው ነበር፤ ኢሳ.1፡11-17 እና ሚል.1፡10 ቢነበብ፣ ጌታ ምን ያህል በዚህ አምልኮ እንደተንገሸገሸ እንረዳለን፡፡ ዛሬም እየሆነ ያለው ይኸው ነው፡፡ በምድራዊ ጣኦቶችና በኀጢአት ተይዘን በዝማሬ ሁካታና ግርግር እግዚአብሔርን ለማደናገር በመሞከር ላይ ተጠምደናል፡፡ እስራኤልና ይሁዳን ይህ በጠላት ምርኮ ከመወሰድ አላዳናቸውም፡፡ እኛም ከመሸነፍ፣ ከመዝቀጥና በሰይጣን ከመማረክ አናመልጥም እየዘመርን ፣ እየጨፈርን! ስለዚህ ንስሐ!www.facebook.com/permalink.php

 
ከእርሱም የሰማናት ለእናንተም የምናወራላችሁ መልእክት። እግዚአብሔር ብርሃን ነው ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም የምትል ይህች ናት።(1ኛ የዮሐንስ መልእክት 1:5)
This website was created for free with Own-Free-Website.com. Would you also like to have your own website?
Sign up for free