እምነት እንጂ ሐይማኖት አያድንም
በወንዱ ብስራት
እምነት እንጂ ሐይማኖት አያድንም፡፡ በአንዳንድ የአማርኛው መፅሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች Faith የሚለው ሐይማኖት በሚል ተተርጉሞአል፡፡ነገር ግን እምነት ተብሎ ቢተረጎም ጥሩ ነው፡፡በዚህ ፅሁፍ ግን ሐይማኖት ስንል religion ለማለት ነው፡፡ በክርስትና ውስጥ እንኩዋ ጊዜ ወለድ የሆኑ ብዙ ሐይማኖቶች አሉ፡፡ ከነኑፋቄዎቹ፡፡ በዋናነት ግን ካቶሊክ፣ኦርቶዶክስ እና ፕሮቴስታንት ይታወቃሉ፡፡ ሁሉም የራሱ በላጭ እንደሆነ ሲሟገት ጌታን እስከመርሳት የተደረሰበት ወቅት አለ፡፡ታዲያ የቱ ይሆን በላጭ እና ቀዳሚ? አጭር ታሪካዊ ምልከታ ወደ ቀደመው መንገድ ይጠቁመናል፡፡
ደቀመዝሙርነት
የተጀመረው በ30 ዓ/ም በገሊላ ነው (ማቴ 4፡18-20)፡፡ ደቀመዝሙር ማለት ተከታይ ማለት ነው፤የሌላውን አስተምህሮ ተቀብሎ የሚኖርበት እናየሚያሰራጭ ነው፡፡ የጌታ ደቀመዝሙር መሆን ማለት እለት እለት ትምህርቱን መከተል፣የህይወት ዘይቤውን መለማመድ፣አስተምህሮውን ማስፋፋት ማለት ነው፡፡
ከደቀመዝሙርነት ባህርያት መካከል ዋናው መታወቂያ ፍቅር ነው (ዮሐ 13፡35)፡፡ ፍቅርባለበት ፍፁም አንድነት መኖሩ ግድ ነው (ዮሐ 17፡20-23)፡፡ “ያመኑትም ሕዝብ አንድ ልብ፣አንዲትምነፍስነበሩአቸው” ሐዋ 4፡32፡፡ ማቴ 12፡25 እንደሚነግረን እርስ በርሱ የሚለያይመንግስት፣ከተማም ሆነ ቤት ፈራሽ መሆኑ ግድ ነው፡፡ ካቶሊክ እንደሐይማኖት ድርጅት ጥንካሬው እንደተጠበቀ በአለም ላይ ለምን ዘለቀ? ኦርቶዶክስ በኢትዮጵያ እንዲሁ ጥንካሬዋ የተጠበቀ ሆኖ ቀጥሎአል፡፡ በሌላ በኩል የፕሮቴስታንት እንቅስቃሴ በአውሮፓ እየተሽመደመደ በኢትዮጵያም እንዲሁ እየተልፈሰፈሰ የመጣው ለምንድ ነው?
ሚስጥሩ ያለው አንድነት ላይ ነው፡፡ ለዚህ አንድነት አስተዋጽኦ ያደረገው ደግሞ ሁለቱም ለሐይማኖታቸው ቀኖና እና ተውፊቶች ጨካኝ የሆኑ ደቀመዛሙርት ባለቤቶች መሆናቸው ነው፡፡ ጋብቻን በሚያህል ጉዳይ ላይ ጨክነው በየዱር ገደሉ እና ገዳማቱ ጭምር ለመኖር የጨከኑ ደቀመዛሙርት ማለቴ ነው፡፡ እነዚህ ደቀመዛሙርት ግን ለመፅሐፍ ቅዱስ እውነታዎች የጨከኑ ናቸው እያልኩ አለመሆኔን ልብ በሉ፣ለሐይማኖታቸው ቀኖና እና ተውፊቶች እንጂ፡፡
የአንድነት ጉዳይ ግን ከፕሮቴስታንቱ ማስተዋል የተሰወረ እውነት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ እንደ ዘመነ መሳፍንት ሁሉም የወደደውንና በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን ለማድረግ ችሎአልና፡፡ አንድነት ባለበት ሁሉ መለኮታዊ ፍቅር ወይም መጽሐፍ ቅዱሳዊው ደቀመዝሙርነት አለ ባይባልም፣አንድነት በሌለበት ግን ፍቅር የለም፡፡ ፍቅር በሌለበት ደግሞደቀመዝሙርነት የለም፡፡
ካቶሊክ
ጅማሬውን በተመለከተ የተለያዩ አመለካከቶች ይንፀባረቃሉ፡-
ሀ/ 270 ዓ.ም.
ለ/ 312 ዓ.ም. ንጉስ ቆስጠንጢኖስ የሮምን ግዛት በአንድ አለምአቀፍ (ካቶሊክ) ቤተ ክርስቲያን ስር የማዋሐድ አላማውን ባሳወቀ ጊዜ
ሐ/ 380 ዓ.ም. ንጉስ ቲዎዶስየስ “ዴ ፊዴካቶሊካ” (De fide catholica) የተሰኘውን እና የካቶሊክ ክርስትናን የመንግስቱ ሐይማኖት የሚያደርገውን አዋጅ ባወጣ ጊዜ
መ/ 384 ዓ.ም.ሲርሲየስ ሊቀጳጳስ (Pontifex Maximus) በሚል በሮምጵጵስና ታሪክ ውስጥ ራሱን ለመጀመሪያ ጊዜ የሰየመበት ወቅት የሚሉ የተለያዩ መራከሪያዎች አሉ፡፡
የሆነው ሆኖ ጽንሱ ቀደም ቢልም በአስተምህሮ ደረጃ ቤተ ክርስቲያን ለሁለት የተሰነጠቀችበት አራተኛው ጉባኤ (ኪልቄዶን) ካቶሊክ እንደ አንድ የሐይማኖት ክፍል ሆና በክርስትና ውስጥ የተወለደችበት ነው፡፡ 458 ዓ.ም. እንደ አውሮፓ አቆጣጠር፡፡
ኦርቶዶክስ
ቃሉ በ325 ዓ.ም. እውነተኛውን እና ቀጥተኛውን የክርስትና ሐይማኖት (ኦርቶዶክስ) ከሐሰተኛው ወይም ከኑፋቄው (ሄትሮዶክስ) ለመለየት ጥቅም ላይ ቢውልም፣አሁን ያለችውን ባለ ብዙ ተውፊትና ዶግማ ዲኖሚኔሽን (ቤተእምነት) ለማመልከት አልነበረም፡፡ በኪልቄዶን ጉባኤ ስለክርስቶስ ምድራዊ ማንነት ክርክር ተደርጎ ነበር፡፡ የሮሙ ፓፓ ሊዮን አንድ አካል ሁለት ባህርይ”ሲል የአሌክሳንደርያው ጳጳስ ዲዮስቆሮስ“አንድ አካል አንድ ባህርይ” አለ፡፡ በዚህም ተወጋግዘው ተለያዩ፡፡
ኦርየንታል ኦርቶዶክስ አብያተክርስቲያናት ዲዮስቆሮስን ሲከተሉ የሮም ካቶሊክና የምስራቅ ኦርቶዶክስ አብያተክርስቲያናት ሊዮንን ተከተሉ፡፡ ኦርቶዶክስ እራሱዋ ሁለት ወገን መሆኗን ልብ ይሉዋል፡፡*
የምስራቅ ኦርቶዶክስ ደግሞ በ1054 ዓ.ም. በተለያዩ ምክንያቶች ከካቶሊክ ተለይታለች፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ቤተ ክርስቲያን ኦሪየንታል ኦርቶዶክስ መሆንዋ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ የኦርቶዶክስ የመጀመሪያው ልደት ያውየኪልቄደን ጉባኤ ሲሆነ አመቱም እንደ አውሮፓ አቆጣጠር 458 ዓ/ም ነው፡፡
ፕሮቴስታንት
ይህ እንቅስቃሴ ቀደምብለው በነበሩ እነ ፒተርዋልዶ (12ኛው ክ/ዘ)፣ጆን ዊክሊፍ (1324-1384)፣ጆንሑስ (1369-1415) ተጠንስሶአል፡፡ ዋና ውልደቱ ግን በማርቲን ሉተር አማካይነት በአውሮፓ አቆጣጠር ጥቅምት 31 ቀን 1517 ዓ.ም. ነው፡፡ ሰው በስራ ሳይሆን በእምነት ብቻ የሚድን መሆኑን ማእከላዊ ሀሳብ ያደረጉ 95 የተቃውሞ አረፍተ ነገሮች(Thesis) በዊተንበርግ ዩኒቨርሲቲ ቤተክርስቲያን ማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ የለጠፈበት ቀን ነው፡፡
ፕሮቴስታንት ካቶሊክን ተቃውሞ የወጣ ነው፡፡ የካቶሊክ ክፋይ፡፡ ይህ ክፍል መፅሐፍ ቅዱሳዊ የሆኑ ዶክትሪኖችን ከ66ቱ መጽሐፍት አንፃር የከለሰ እና የቀረፀ ቢሆንም በጥቃቅን ልዩነቶች በመከፋፈልና በመበጣጠቅ ይታወቃል፡፡ ክፍፍል በመጨረሻው በፕሮቴስታንቱ ውስጥ ሊቀለበስ በማይችል መልኩ ሕጋዊ እና መንፈሳዊ መልክ ተላብሶአል፡፡ ለወንጌል አመቺ ነው በሚል ፈሊጥ ፡፡ ግን መፅሐፍ ቅዱሳዊ መሰረት የሌለው አባባል ነው፡፡ጌታም ሆነ ሐዋርያት ለወንጌል ስራ አመቺ እንደሆነ የነገሩን አንድነትን እንጂ መከፋፈልን አይደለም፡፡ ይልቁንም መለያየት የስጋ ስራ እንደሆነ በግልፅ መፅሐፍ ቅዱስ ይነግረናል ገላ 5፡20፤ዮሐ 17፡20-21፤ኤፌ 4፡3፤13፡፡
ለማንኛውም እርስ በርሱ የሚከፋፈል ቤት፣ከተማም ሆነ መንግስትፈራሽ እንደሆነ ማቴ 12፡25 በግልፅ ያስቀመጠው ለፕሮቴስታንቱም የግድ ይሰራል፡፡ ለዚህ ነው ይህ እንቅስቃሴ በአውሮፓ እየከሰመ የመጣው፡፡ በሌሎች ስፍራዎችም ክፍፍሉ እልባት ካልተገኘለት ይፈርሳል፣ ማለትም ተራ ሐይማኖት ሆኖ ይቀራል፡፡ ልብ ማለት ያለብን ግን የእግዚአብሔር መንግስት በትውልድ ይቀጥላል እንጂ አይቋረጥም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች በታጠቀ እና በሐይማኖታዊ ግሳንግስ ባልታሰረ ትውልድ ወንጌል ማሸነፉን ይቀጥላል፡፡ የተሸነፈው የሰው እጅ ስራ የተቀየጠበት ሐይማኖት እንጂ ክርስትና አለመሆኑን ልብ ልንል ይገባል፡፡ ክርስትና አይሸነፍም፡፡ ሐይማኖት እና ሐይማኖተኞች አንድ ቀን በዓለም፣በስጋና በሰይጣን ትብብር ይሸነፋሉ፡፡ ደቀመዛሙርትና መጽሐፍ ቅዱስ ግን ተሸንፈውም አያውቁ፣አይሸነፉምም፡፡
እንግዲህ ነገራችንን እንደሚከተለው፣መደምደም ይጠበቅብናል፡-
ሀ/ ክርስቲያን ከሆንክ
በያዝከው ሐይማኖት ትኩራራ ዘንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ አይኖርህም፡፡ሐይማትህን ከሌላው ለማስቀደም ወደ 33 ዓ/ም (ከበዓለኀምሳ ቀን ጋር) ታጠጋጋው ይሆናል፡፡ ያምእንኩዋ ቢሆን በ30 ዓ/ም በማቴ 4፡18-20 ላይ ተጀምሮ በማቴ 28፡18-19 (በዓለኀምሳንቀድሞ) የታዘዘው ደቀመዝሙርነት ይቀድምሃል፡፡
በማቴ 28፡18-19 ደግሞ ጌታ ያዘዘን ህዝቦችን ወደ ደቀመዝሙርነት እንድንጠራ እንጂ ከላይ ወደ ጠቀስናቸው ቤተ እምነቶች አባልነት አይደለም፡፡ የነዚህ አብያተ እምነቶች አባል መሆን ኃጢአትባይሆንም ወደ ደቀመዝሙርነት መመለስ ግን ግድ ይለናል፡፡ አንድነትና ፍቅር በሌለበት ደቀመዝሙር እንደሆንን ብንከራከር ግን አያዋጣንም፡፡ መታወቂያው የለንምና፡፡
ከላይ የተጠቀሱት ሐይማቶች፣የሚያቀራርቡን ብዙ ነገሮች ያሉን ነን፡-
በአብ፣በወልድ፣በመንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ መጠመቅ
በጌታ አስተምህሮ ወይም በ66ቱ የቀኖና መጽሐፍት
በ3ቱ የመጀመሪያ የቤተክርስቲያን ጉባኤያት (ኒቀያ፣ቁስጥንጥንያ እና ኤፌሶን) አንለያይም፡፡ ታዲያ መናቆሩን ትተን ወደ ቀደመው የደቀመዝሙርነት መንገድ ብንመለስስ? ልብልንል የሚገባን 3ቱም ሐይማኖቶች የስነመለኮታዊ ክርክሮች ውጤት ሲሆኑ ደቀመዝሙርነት ግን የራሱ የጌታ ትዕዛዝ ነው፡፡ ስለዚህ ለክርስቲያኑ፣ ዛሬም ጌታ በሉቃስ 14፡25-33 ያለውን ጥሪ ያቀርባል፡፡ ከሐይማኖት ቀናዒነትና ከተውፊት አፍቃሪነት ይልቅ ወደ ደቀመዝሙርነትና ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ቀጥተኛ ትርጓሜ እንድንመለስ፡፡
ለ/ ክርስቲያን ካልሆንክ ለአንተም ጥሪ አለ፡፡ በዚያው ሉቃስ 14፡16-24 ያለው ጥሪ ይመለከትሃል፡፡ “ኢየሱስም፡- እኔ መንገድና እውነት፣ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” ሲል ወደ ፈጣሪ መድረሻ ብቸኛ መንገድ እርሱ እንደሆነ ይነግርሃል ዮሐ 14፡6፡፡ ደግሞም፡- “በሩ እኔ ነኝ፤በእኔ የሚገባ ቢኖር ይድናል” ይልሃል ዮሐ 10፡9፡፡ “በእርሱ የሚያምን አይፈረድበትም፤በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል” ሲል ፍርድ እንዳለ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል (ዮሐ 3፡18)፡፡ እግዚአብሔርስለሚወድህ አንድ ልጁን ወደ አለም ልኮ ስጋ በማልበስ በመስቀል ላይ ስለአንተ ሐጢአት እንዲቀጣ አድርጎታል፡፡ ፍቅሩን ቸል ብትል ግን ከዘለዓለም ፍርድ አታመልጥም፡፡ ስለዚህ ንስሐ ገብተህ በአዳምና ሔዋን ምክንያት ከመጣብህ ጥፋት ልታመልጥ ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ አጭሩ መንገድ በእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ጌትነት እና አዳኝነት ማመን ነው፡፡ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና” ዮሐ 3፡16፡፡
የደቀመዝሙርነት ዋጋ
ሉቃ 14፡25-43
ደቀመዝሙር ስለ ኢየሱስ ፍቅር፡-
አባቱን እና እናቱን
ሚስቱን እና ልጆቹን
ወንድሞቹን እና እህቶቹን
የራሱን ህይወት እንኩዋ ሳይቀር የጣለ ነው፡፡ ይህ ማለት ቃል በቃል ጥላቻ ሳይሆን ስለ ጌታው ሁሉን የተወ፣ሌሎችን በክርስቶስ ፍቅር የሚወድ፣ነገር ግን የእነርሱ ፍቅር ከጌታው የማይበልጥበት ማለት ነው፡፡ ስለራሱም ቢሆን ጌታውን መከተሉ ሞት ቢጠይቀው እንኩዋ መስቀሉን ተሸክሞ የሚከተል ነው፡፡
አንድ ሰው ሲናገር እንደሰማሁት ይህ ትውልድ እግዚአብሔርንም፣ ዓለምንምበጣም ይወዳል፡፡
ዓለምንመውደድ የእግዚአብሔር ጠላትነት ምልክት ነው (1ዮሐ2፡15-17፤ያዕ 4፡4)፡፡ እናም በእንዲህ አይነት መንታ ፍቅር ተነድፈንደቀመዝሙርነት የማይታሰብነው፡፡የምድሩም ሆነ የሰማዩ፣ስጋዊውም ሆነ መንፈሳዊው እንዳይቀርብን እያለቀስን ደቀመዝሙር መሆን ዘበት ነው፡፡ የልባችንን ዝንባሌ ፈትሸን የሚያስከፍለንን ዋጋ ተምነን ደቀመዝሙር ብንሆን ይሻላል፡፡
ዋቢ**
ቀሲስ ምክረስላሴ ገ/አማኤል (ዶ/ር)፣የእግዚአብሔር መንግስት ታሪክ በምድር ላይ (ጠቅላላ የቤተክርስቲያን ታሪክ)፤ ሁለተኛ መጽሐፍ፣ብርሐንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት፣አዲስ አበባ፣2002 ዓ/ም፡፡
አባ ጎርጎርዮስ (M.A)፣የሸዋሊቀጳጳስ፣የቤተክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ፣ትንሳኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት፣አዲስ አበባ፣1978 ዓ/ም፡፡
ጄ.ሲ.ዊንገር (ትርጉም ካሱ ከበደ)፣የክርስቲያን እምነት፣የቤተክርስቲያን ታሪክ ውልብታ፣ርሆቦት አታሚዎች፣አዲስ አበባ፣1998 ዓ/ም፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ፣የ1952 አማርኛው እትም፡፡
“History of the orthodox church,”Wikipedia; the free encyclopedia. Wikimedia foundation, inc.16 may 2013. Web.(Retrieved) 8 August 2013.<http;//en. Wikipedia. Org/wiki/History-of- the –orthodox-church>
“Eastern Orthodox church.”Wikipedia; the free encyclopedia.Wikimedia foundation, inc. 5 aug. 2013.Web.8 August 2013.<http;//en.wikipedia. Org/wiki/eastern-orthodox-church>
“History of oriental orthodoxy.”Wikipedia; the free encyclopedia. Wikimedia foundation, inc.26 june 2013, web.8 August 2013. <http;//en.wikipedia.org/wiki/History-of oriental-orthodoxy>
“History of the catholic church.”Wikipedia; the free encyclopedia. Wikimedia foundation, inc.3 july 2013. Web.8 August 2013.< http;//en. Wikipedia. Org/wiki/ History-of-the-catholic church>
“Disciple (Christianity). “Wikipedia; the free encyclopedia. Wikimedia foundation, inc. 6 july 2013. Web 8 August 2013. <http;//en. Wikipedia. Org/wiki/Disciple-(Christianity)>
Laude, Summa C. “THEBEGINNING OF THE ROMAN CATHOLIC CHURCH.” www.Theology web. Com. 23 july 2005. Retrieved 8 August 2013.<http;// www.theology web. Com /Campus/ shows thread. Php? 58060- THE-BEGINNING-OF-THE-ROMAN-CATHOLIC-CHURCH>
¬
*ኦሪየንታል ኦርቶዶክስ የተባሉት የኢትዮጵያ፣የኤርትራ፣የግብጽ፣የአርመን፣የሶሪያ እና የህንድ ኦርቶዶክስ አብያተ ቤተክርስቲያናት ናቸው፡፡የምስራቅ ኦርቶዶክስደግሞ የግሪክ፣ሜቄዶኒያ፣ሞልዶቫ፣ዩክሬን፣ቤላሩስ፣ጆርጂያ፣ሩሲያ፣ሰርቢያ፣ሮማንያ፣ቡልጋሪያ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናትን ያጠቃልላል፡፡
**ዊኪፔዲያ ያለቀለት የመረጃ ምንጭ ባይሆንም የሌሎች ዋቢዎች ምንጭ ነውና በዚሁ መልክ ልንጠቀምበት ይገባል፡፡